በትግራይ ክልልል ማእከላዊ ዞን አክሱም ከተማ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሂጃብ ጋር በተያያዘ እንዳይፈተኑ ተደረጉ፡፡ ተማሪዎቹ ከዚህ በፊት በሂጃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ለ8 ወራት ያህል ከትምህርት ተገልለው የቆዩትን እነዚህን ተማሪዎች በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የ12ተኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን እንዲፈተኑ ፎርም ማስሞላቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በተጀመረውና በአክሱም ከተማም እየጠሰጠ ባለው በዚህ ፈተና ላይ እነዚህ ተማሪዎች እንዳይፈተኑ ተደርገዋል፡፡
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት የእነዚህ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች አድሚሽን ካርድ ዘግይቶ የደረሰው በመሆኑ በሁለተኛው ዙር እንዲፈተኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ኪሮስ ይህንን የሚገልፅ ሀሳብ በትግርኛ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ ፅፈዋል፡
በመጪው ሀሙስ በሚጀመረው ሁለተኛ ዙር ፈተና ላይ እነዚህን ተማሪዎች ለማስፈተን ጥረት እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአክሱም ከተማ ከዚህ ቀደም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሂጃብ ጋር በተያያዘ ምክንያት የ8ተኛ ክፍል ፈተናን ሳይፈተኑ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡
(ዘ-ሐበሻ)
