የሀገሪቱ የመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 9.4 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህም ካለፈው የየካቲት ወር 2018 ዓ.ም የዋጋ ግሽበት መጠን (9.7 በመቶ) ጋር ሲነፃፀር የ0.3 በመቶ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ቢሆንም፣ የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች ዋጋ ግሽበት ግን ካለፈው ወር የ10.8 በመቶ ጭማሪ ወደ 11 በመቶ ከፍ ብሏል።
በዚህም መሠረት በምግብ ዘርፍ ላይ የ0.2 በመቶ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆነው የዋጋ ግሽበት ደግሞ 7 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
ምግብ ነክ ባልሆኑ ዘርፎች ውስጥ የታየውን የዋጋ ጭማሪ በዝርዝር ሲታይ፣ ከፍተኛው ጭማሪ በልዩ ልዩ እቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የ15 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። በመቀጠልም በትራንስፖርት 13 በመቶ፣ በልብስና ጫማ 11.3 በመቶ፣ እንዲሁም በምግብ ቤቶችና ሆቴሎች 10.5 በመቶ ጭማሪ ታይቷል።
በተጨማሪም በኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ 8.6 በመቶ፣ በቤት እቃዎች 8.2 በመቶ፣ እንዲሁም በአልኮል መጠጦችና ትምባሆ ላይ የ7.6 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መመዝገቡን መረጃው ያመላክታል።
