በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ሽፋን በተፈጸመ የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮችን ጉዳይ ለመመልከት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለፖሊስ የ8 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።
ባለፉት 12 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለችሎቱ ያስረዳው ፖሊስ፣ በተለይም 12 የመንግስት እና የግል ሚዲያዎች እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ባንኮች ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ መረጃ በጽሁፍ እንዲልኩ መጠየቁን፣ እስካሁን የ150 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ጠቅሶ ከወንጀሉ ውስብስብነትና ስፋት አንፃር ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።
በተቃራኒው የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ደንበኞቻቸው በህዝብ ዘንድ የሚታወቁና ቋሚ መኖሪያ ያላቸው መሆኑን እና የራሳቸው መተዳደሪያ ስራ ያላቸውና አብዛኞቹም የጤና እክል ያለባቸው ናቸዉ በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ተከራክረዋል።
ባለፈው የችሎት ውሎ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በድርጊቱ ውስጥ የነበረውን የግል ተሳትፎ እና የጥቅም ትስስር የሚገልጽ ማብራሪያ ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ በዛሬው ዕለት በሰጠው ትዕዛዝ ፖሊስ የቀረውን ምርመራ አጠናቆ እንዲያቀርብ 8 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።
ተጠርጣሪዎቹ ለቀጣይ የችሎት ቀጠሮ ሚያዝያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲቀርቡ አዟል።
ሸገር 102.1
