በኢትዮጵያውያን የተሰራው የእንሰት ምርምር እና ፈጠራ ስራ ውጤት በኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ (STI) 2025 ፎረም ላይ ግንቦት 9 ቀን 2025 በተሞክሮነት ቀርቧል።
በዶ/ር አዲሱ ፍቃዱ የሚመራው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቡድን እንሰትን ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ ምግብ በመቀየር የሚያስችሉ አዳዲስ የምርምር እና የፈጠራ ውጤቶችን በተሞክሮነት አቅርበዋል።
ይህ ፈጠራ በዋናነት ከእንሰት እሴት የተጨመረባቸው ምግቦችን ማምረት የሚያስችል የምርምር እና የፈጠራ ስራ ውጤት ሲሆን፤ ምርቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ፍላጎት እየጨመረ የመጣውን የእንሰት ምግቦችን ለማሰተዋውቅ ያለመ ነው፡፡
በተጨማሪም፣ ይህ ፈጠራ የተባበሩት መንግስታት የ2030 የልማት ግብ ለማሳካት የሚከናወኑ ስራዎችን በሳይንስ እና በፈጠራ ስራ በማገዝ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ፤ ፈጠራውም የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) ማለትም Zero Hunger (SDG 2)፣ Good health and wellbeing (SDG 3)፣ Gender Equality. (SDG 5)፣ Decent Work and Economic Growth (SDG 8)፣ Climate action (SDG 13) እና Partnership for the Goals (SDG 17) በቀጥታ ተደራሽ በማድረጉ ለሌሎች ሀገራት በተሞክሮነት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
ይህ ስራ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓለም ዓቀፍ የዘረመል እና ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል፤ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቱት፣ በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ የተከናወነ ነው፡፡
