የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ከሐምሌ 2017 ዓ/ም ወዲህ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት ከ288,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታወቀ።
የሶማሌ እና የኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪዎች የተፈናቃዮቹን ቁጥር ለግምጋሚ ቡድኖች አረጋግጠዋል። ይህ ግጭት በ1997 ዓ.ም. ከተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ጀምሮ ባልተፈቱ የግዛት ጥያቄዎች እና በተደጋጋሚ በሚከሰት በአነስተኛ የተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚደረጉ ግጭቶች ምክንያት የተከሰቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች ባስከተሉት የጅምላ መፈናቀል ምክንያት፣ እስከ 2011 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አፈናቅለዋል ተብሏል።
ከአጎራባች ሶማሌ ክልል በሚመጡ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በተፈጠረ ግጭት፣ የሰባት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉንና ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል። በሶማሌ ክልል የኡዴት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንና ብዙ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል።
የፀጥታ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን እና በአጎራባች ሶማሌ ክልል ወረዳዎች መካከል በሐምሌ ወር ለተቀሰቀሰው የድንበር ግጭት መፍትሔ የሰላም ውይይት መጀመራቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ፣ ነዋሪዎች በሂደቱ ውስጥ አለመካተታቸውን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፤ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች በመጠለያ እጥረት እና በቂ ባልሆነ የጥበቃ አገልግሎት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ብሏል። የደህንነት ስጋቶችም የበቀል እርምጃን፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ እና ቀጣይነት ያለው የደኅንነት እጦትን ያካትታሉ ሲልም አክሏል። የማኅበረሰብ መሪዎች እንደገለጹት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች በሰላም ለመኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፣ ነገር ግን ወደ ቀዬአቸው ከመመለሳቸው በፊት የደኅንነት ማረጋገጫዎች ያስፈልጋቸዋል።
በተጎዱት አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኖሩ ተገልጿል፤ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የውኃ እጥረት፣ ዝቅተኛ የክትባት ሽፋን እና ውስን የሆነ የጤናና የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎት ተላላፊ በሽታዎች የመከሰት ስጋትን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል ተብሏል። በተጎዱ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች በመሠረተ ልማት መጎዳት፣ በአስተማሪዎች መፈናቀል እና ትምህርት ቤቶች ለጊዜያዊ መጠለያነት በመዋላቸው ትምህርት አቋርጠዋል ተብሏል።
በኦሮሚያ ክልል፣ በምስራቅ ቦረና ዞን አሬሮ፣ ዳስ፣ ጉሚዳሎ ኦና ዋጪሌ ወረዳዎች ውስጥ 151,972 ሰዎች ተፈናቅለዋል። የአካባቢው ባለሥልጣናት የሰው ሕይወት መጥፋትን ጨምሮ፣ ከ5,700 በላይ ከብቶች መዘረፋቸውን እና ሰፊ የንብረት ውድመት መድረሱን ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል የዞን ባለሥልጣናት ደግሞ፣ በዳዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሞያሌና ኡዴት ወረዳዎች፣ እንዲሁም በሊበን ዞን በሚገኙ ደካሱፍቱና ከርሳዱላ ወረዳዎች ውስጥ 136,199 ሰዎች ተፈናቅለዋል ሲሉ ገልጸዋል። በነሐሴ ወር በተካሄደው ግምገማ (MIRA) በሞያሌ (57,600)፣ በኡዴት (45,000)፣ በከርሳዱላ (21,500) እና በደካሱፍቱ (12,000) ተፈናቃዮች እንደሚገኑ ተረጋግጧል። የአካባቢው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤቶች የንብረት መውደምና መቃጠል፣ የከብቶች መዘረፍ፣ እና በርካታ ሰዎች መገደልና መቁሰል ክስተት ተመዝግቧል ብለዋል።
ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ኤጀንሲዎች ምግብ፣ መጠለያ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ የውኃና የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ፣ የተመጣጠነ ምግብ አገልግሎቶች እና በተለይም ለሴቶች ደኅንነት መብራት፣ እንዲሁም ልብስ፣ ጫማና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።አስ
