የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን 111 የኤርናቪጌሽን ባለሙያዎችን አስመረቀ።
ባለስልጣን መስሪያቤቱ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ተማሪዎችን ላለፉት ስምንት ወራት በተለያዩ የኤርናቪጌሽን አገልግሎት የሙያ መስኮች ያሰለጠነ ሲሆን ነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ.ም አስመርቋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ “ተቋምን ለመገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል እድል ሊያገኙ ይገባል፤ እኛም የኢትዮጵያን ብዝሀነት ተቀብለን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተቋማት ውስጥ እኩል የመቀጠር መብትና እድሉን እንዲያገኙ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።
ዶ/ር አለሙ አያይዘውም በህዳሴው ግድብ ምርቃት ዋዜማ ላይ ስለደረስን እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉ ሲሆን የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ የህዳሴው ግድብ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲያገኝ፤ በታለመለት የጥራት ደረጃና ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና የተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ሀገር የመረከብና ዘርፉን ለማሳደግ የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ አበራ በበኩላቸው ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የመንግስትን አቅጣጫ ተከትሎ ሪፎርም እየሠራ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ 2026 እ.አ.አ የአለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚያደርገው ሙሉ ኦዲት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋው ተመራቂዎችም መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል።
