ንቃቃት የበዛው የትምህርት ገበታ!

Date:

ሀገራችን እንከን የበዛው የትምህርት ሥርዓትን ስትከተል ረዘም ያሉ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ ደግሞ በመሠረተ ልማት እጥረትም የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ተፈትኖ ቆይቷል፡፡ የለውጡ መንግሥት ወደ አመራር በመጣ ማግሥት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በሥራ ላይ ውሎ ነበር፡፡ ለአዲሱ ፍኖተ ካርታ ስኬታማነትም የትምህርት ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪና ጉትጎታዎች ሲደረጉ ነበር። በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ የነበሩት ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መኾናቸውን አንስተው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ ይህን ያሉት አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ይኾን ዘንድ 2011 በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነበር፡፡

ሚኒስትሩ በወቅቱ ችግሩን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል የትምህርት ባለሙያ በበቂ ሁኔታ አለመፈጠሩን አንስተው በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱና አተገባበሩ በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱን ለተወሳሰበ ችግር ሊያጋልጣት እንደሚችል ጠቁመው ነበር። የትምህርት ጥራቱ ትልቁ ችግር የገንዘብ ሳይኾን የቅንጅትና የቀናኢ አስተሳሰብ እጦት በመኾኑ ችግሮቹን ለመፍታት በጋራ መሥራት ይጠበቅናል ያሉት የወቅቱ ሚኒስቴር ዲኤታ፣ አዲሱ የትምህርትና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ የውጭ ተሞክሮዎች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥመው የሚተገበሩበት መኾኑን አስረድተው ነበር። ከዓመታት በኋላ የዚህን እቅድ አፈጻጸም ዞረን ስናየው ምንም ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ለውጥና መሻሻል ላለማምጣታችን ምክንያቱ ግን ባለሥልጣኑ እንዳሉት ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር ብቻ ሳይኾን ችግሩን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል የትምህርት ባለሙያ በበቂ ሁኔታ አለመኖርና የተከተልነው ፍኖተ ካርታ ሚናው ከፍ ያለ ሳይኾን አልቀረም፡፡ ያኔ በተደሰኮረው ልክ በተሻለ መንገድ ለውጤታማነቱ ተሠርቶ ቢኾን ይሄኔ የት በደረስን ነበር፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ለትምህርት ጥራት መውረድ መምህራንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው ቀርቧል፡፡ እንደእውነታው ይህን ዓይነት ሕግ መውጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት አንዱ ድክመት በመማር ማስተማር ሂደት ለሚመጣ ውድቀት ተጠያቂነት አለመኖር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለፉትን ሁለትና ሦስት ዓመታት ይህ ሁሉ ተማሪ ከማትሪክና ከሚኒስትሪ ሲወድቅ አንድም ተጠያቂ አካል አለመኖሩ አስገራሚ ነበር፡፡ ይህ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ ሕግ በአገር አቀፍ፣ በክልል ወይም በአካባቢ ደረጃ ያለው የትምህርት ደረጃና ጥራት ከተጠበቀው በታች መውረዱ ሲረጋገጥ የሚመለከታቸው የፌደራል፣ የክልልና የአካባቢ የትምህርት አስተዳደር ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ማለት ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በመማር ማስተማር ሂደቱ ዙሪያ ለሚመጣ ማናቸውም ቀውስ እንደእስካሁኑ ተማሪን መኮነን ብቻ ሳይኾን ሁሉም የሚመለከተው ባለድርሻ አካል የሚጠየቅበት ፍትሐዊ አግባብ ሰፈነ ማለት ነው፡፡

የትምህርት ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ለሰው ሀብት ልማት የሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ በአብላጫ ድምፅ ተመርቷል፡፡ ይህ ለዝርዝር ውይይት የተመራው ረቂቅ ሕግ የትምህርት ደረጃና ጥራት ከሚጠበቀው በታች የወረደ መኾኑ ሲረጋገጥ የትምህርት ተቋሙ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መምህራን፣ ሌሎች ለችግሩ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትና ግለሰቦች ተጠያቂዎች እንደሚኾኑ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በረቂቅ ሕጉ ላይ በመማር ማስተማር ሒደቱ የትምህርት ደረጃና ጥራት መርማሪዎችን ሥራ ለማስተጓጎል የሚደረጉ ተግባራት የተከለከሉ መኾናቸው የተደነገገ ሲኾን፣ የአጠቃላይ የትምህርት ደረጃ ጥራትን በባለቤትነት የሚያስጠብቅ የትምህርት ቁጥጥርና ክትትል አገልግሎት የሚሰጥ መንግሥታዊ ተቋም በትምህርት ሚኒስቴር ሥር እንደሚቋቋምም ተካቶበታል፡፡

ረቂቅ ሕጉ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ማንኛውም ሕፃን ለአጠቃላይ ትምህርት ያለውን መብት ተግባራዊ ማድረግን የሚጠቁም ሲኾን ተማሪውም በበኩሉ የአንደኛና መለስተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ያለበትን ግዴታ መወጣቱን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በትምህርት ዘርፍ ለሚሳተፉ ባለሀብቶችና ሌሎች መንግሥታዊ ላልኾኑ አካላት በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ሕግና አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት ማበረታቻ እንደሚሰጥም ተቀምጧል፡፡ በረቂቁ መሠረት የቅድመ አንደኛ ደረጃ መግቢያ ከአራት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ሲኾን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዕድሜ ደግሞ ሰባት ዓመት ተደርጓል፡፡ ተማሪዎች ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ እንደሚደረግ የተደነገገ ሲኾን፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም አንድ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ ክልሉ በሚመርጠው መሠረት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ በአማራጭነት እንዲሰጥ እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡

ኾኖም ይህኛውን ድንጋጌ በተመለከተ ግን ከምክር ቤቱ አንዳንድ አባላት ከፍ ያለ ተቃውሞና ትችት ገጥሞት ነበር፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዙሪያ ከሦስት በላይ የምክር ቤት አባላት የትምህርት ጥራት በቀጥታ ከመምህራን ጥራት ጋር አገናኝተው ሃሳባቸውን በተቃውሞው በኩል ሰጥተዋል። ለምሳሌ በመምህራን የሚቀርቡ ጥያቄዎችንም አዋጁ የሚያስተናግድበት መንገድ እንዲፈጠር የጠየቁት የምክር ቤት አባሉና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የኾኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው “የመምህራንን የኑሮ ሁኔታ ሳናሻሽል እንዴት አድርገን ነው የትምህርት ጥራትን የምናሳካው? ስለሚበላው ነገር የሚያስብ፤ የት እንደሚያድር የሚያስብ መምህራንን ይዘን እንዴት ነው ረቂቁን ተግባራዊ የምናደርገው? አሁንማ በሚገርም ሁኔታ ወሩን ጠብቆ ደሞዝ ስላልመጣ ሲያምጽ፣ ተቃውሞ ሲያሰማ የሚታሰርባቸው ክልሎች መኖሩን በተለያዩ ሜንስትሪም ሚዲያዎች የምንሰማበት ነውና የመምህራንን የትምህርት ጥራት ሳናሻሽል የትምህርት ጥራትን ማሳካት አንችልም። ግብዓቶችን በጥቂቱ ሳናሟላ ውጤት መጠበቁ እንደማያዋጣ አያዋጣም። ለትምህርት ጥራቱ ብዙ ነገሮች መታየት አለባቸው።” ሲሉ አጠቃላይ የረቂቁን ተግባራዊነት ነቅፈዋል፡፡

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ከአፍ ቋንቋቸው ውጪ “ከፌደራል የሥራ ቋንቋ አንድ መርጠው እንዲሰጡ” የሚለው አገላለጽ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለው መኾኑን ዶ/ር አበባው አንስተዋል። ዶ/ር አበባው “ሕገመንግሥቱ ይሻሻል ችግር የለውም፤ ዜጎች በቋንቋቸው የመማር መብታቸው ይከበር። በጣም የሚበረታታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን ሳናሻሽል 5 የሥራ ቋንቋዎች ውስጥ ምረጡ ማለት አስቸጋሪ ነው።” ሲሉ ጥቅል አካሔዱንም ተችተዋል። በተመሳሳይ ቋንቋን በተመለከተ ሀሳባቸውን የሰጡት የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ አቡኔ ዓለም በተለይ ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ጋር በተያያዘ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩና ማብቂያውን በክልሎች እንዲወሰን በረቂቅ አዋጁ መቀመጡ የብሔረሰብ አስተዳደሮችን መብት የሚጋፋ እንደኾነ አስረድተዋል። ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ሲቲ ሬዲዋንም የአፍ መፍቻ ቋንቋ በክልሎች መወሰኑ “የዚያ አከባቢ ሰው ከሌለ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ” ሲሉ ለክልሎች ኃላፊነቱ መሰጠቱን ተቃውመዋል። ማሳያ ይኾናቸው ዘንድም የወለኔ ሕዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው የመማር እድል አለማግኘቱን እንደአብነት ጠቅሰዋል።

ወደ ረቂቅ ሕጉ ስንመለስ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ ወንጀል ፈጻሚው አካል በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መኾኑ ከተረጋገጠ በማንኛውም የአጠቃላይ ትምህርት ተቋም መምህር ኾኖ ለመቀጠር እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም ሰው ተገቢው የማስተማር ሥራ ፈቃድ ሳይኖርው በአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በመምህርነት ሊሠራ እንደማይችል በረቂቁ ላይ የተቀመጠ ሲኾን ለዚህ የሚረዳና የሥራ ፈቃድ አሰጣጥን የተመለከተ የስታንዳርድ መመርያ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እንደሚወጣም በረቂቁ ላይ ሰፍሯል፡፡ ከቅድመ ሥራ ሥልጠና በኋላ በመምህርነት የሚመደብ ሰው በቅድሚያ የሁለት ዓመት የትውውቅ ሥልጠና የመከታተልና ለዚህም የሚሰጠውን መመዘኛ ፈተና የማለፍ ግዴታ እንዳለበት የሚጠቁመው ረቂቅ ሕጉ ይህን ግዴታ ከተወጣ የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ የመምሀራን የሙያ ፈቃዱ በየሁለት ዓመቱ የሚታደስ ሲኾን ዕድሳቱ ከማንኛውም የፈቃድ ክፍያ ነፃ ተደርጓል፡፡ ይህ ዕድሳት ለመምህራን ደረጃ ዕድገት እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡

የትምህርት ክፍያ አለመኖርን በተመለከተ በሚያብራራው አንቀጽ ላይ ደግሞ በማንኛውም የመንግሥት አጠቃላይ የትምህርት ተቋም ውስጥ በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ከሚማር ተማሪ ከወላጆች ወይም ከአሳዳሪዎች የትምህርት ክፍያ፣ የመማርያ መጻሕፍት ዋጋ ወይም የመመዝገቢያ ክፍያ መቀበል ክልክል መኾኑ ተደንግጓል፡፡ መንግሥት ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትን በብቃትና በጥራት ለማዳረስ ያለውን ግዴታ በሚገባ እንዲወጣ ያስችለው ዘንድ፣ አገር አቀፍ የትምህርት ፈንድ እንደሚቋቋም በረቂቁ ተካቷል፡፡ በውጭ አገር ማኅበረሰቦች የሚቋቋሙ ትምህርት ቤቶችም ከሚያስፈልጋቸው በጀት በአገራቸው መንግሥት 30 በመቶ የሚደገፉ እንዲኾኑ፣ ቀሪውን 70 በመቶ ራሳቸው መሸፈን የሚችሉ መኾናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ማምጣት እንዳለባቸውም በረቂቁ ላይ ሰፍሯል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቋቋሙ የውጭ አገር ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶችና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ከሚመለከተው አገር የሥራ ፈቃድ ማምጣት እንደሚገባቸውም ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው የትምህርት ሥርዓት እየተፈተ ያለው በጽሑፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው በጥራት ብቻ ሳይኾን በጦርነት ሳቢያ በተደራሽነትም ጭምር እየኾነ መጥቷል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትምህርት የፖለቲካ መሣሪያ እየኾነ በመምጣቱ ለሌላ ተግዳሮት ተዳርጓል፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች በተከሰቱ እና በቀጠሉ ግጭቶች እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት 5 ሺሕ 568 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ እንደሚታወቀው የእነዚህ ግጭቶች ዋነኛው መንስኤ ፖለቲካ ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ግጭት የፖለቲካ ጥያቄን በመሣሪያ ለማስመለስ የሚደረግ ትግል ነው፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ደግሞ ትምህርት በመንግሥትም ይኹን በተዋጊ ኃይሉ በኩል በተለይም ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ ይገኛል፡፡ መንግሥት አማጽያኑ ተማሪዎች እንዳይማሩ “ቀሰቀሰ” አልፎም “የጸጥታ ስጋት ኾነ” በሚል ሲከስ አማጺያኑ ደግሞ “መንግሥት ትምህርት ቤቶችን በከባድ መሣሪያ እየደበደበ የመማር ማስተማር ሂደትን መከወን አይቻልም” ሲሉ ይከሳሉ፡፡  

ኢሰመኮ በሪፖርቱ በትግራይ ክልል 105 ገደማ ትምህርት ቤቶች በጦርነት በመውደማቸውና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በመኾናቸው ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አለመኾኑን ገልጾ እንዲሁም ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 52፣ በአፋር ክልል 17፣ በአማራ ክልል 14፣ በኦሮሚያ ክልል 11፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 11 እና በጋምቤላ ክልል 11 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አስታውቋል። ኢሰመኮ መረጃውን ጠቅለል አድርጎ ሲያቀርበው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ እና በቀጠሉ ግጭቶች እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት፤ በአማራ ክልል 4 ሺሕ 178፣ በትግራይ ክልል 648፣ በኦሮሚያ ክልል 420፣ በሶማሊ ክልል 195፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 50፣ በጋምቤላ ክልል 40፣ በአፋር ክልል 26 እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 8 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አመላክቷል፡፡ የጸጥታ ሁኔታው አንጻራዊ መሻሻል ባሳየባቸው አካባቢዎች ደግሞ መምህራን አካባቢውን ለቀው የሄዱ በመኾናቸው የመምህራን እጥረት መኖሩን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በአካባቢዎቹ አስተማማኝ ጸጥታ ባለመኖሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንደማይልኩ ጠቁሞ በተለይ “በአንዳንድ አካባቢዎች መምህራን ትምህርት ቤት ውስጥ ለመገኘት በተለይም ሴት መምህራን የመደፈር እና የመዘረፍ ሥጋት ያለባቸው በመኾኑ ትምህርት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲል ገልጿል።

በጥቅሉ አሁንም ትምህርትን የተመለከተ ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ መኾን ይኖርበታል፡፡ የጸጥታ ችግሩም ይሁን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ላይ በትኩረት ሠርቶ የቀጣዩን ትውልድ እጣ ፋንታ ማስተካከል ይገባል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን የኑሮ ሁኔታ፣ ክህሎትና የስራ ዲሲፕሊን እንዲሁም የሥራ አካባቢን ማሻሻል፤ እንዲሁም የጸጥታ ችግርን ለመቅረፍ ተፋላሚ ኃይሎች ኃላፊነት የሚወስዱበት ሁኔታን መፍጠር ይገባል። የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት በቂና ብቁ መምህራንን ማፍራት ተገቢ ነው። በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት እርከኖች ለትምህርት ጥራት ወሳኝ የኾኑ መምህራንን በብዛትና በብቃት ለማፍራት ትኩረት መስጠት ይገባል። ተማሪን ያማከለ ዘመናዊና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደት መከተል፤ የመምህራን ጥራትና ተነሳሽነት ማጎልበት፤ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል፤ ተማሪዎችን ማነቃቃት፤ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራርን ማብቃት፤ ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፤ የማስተማሪያ ግብዓቶች ማሟላትና እንዲሁም የተማሪዎች ሥነ ምግባርን ማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዋነኛው መንገድ ነው።

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...

ከ 50 ሚሊዮን በላይ መራጮች በማንዋልና በዲጂታል ተመዝግበዋል

ከየካቲት 28_መጋቢት 28 የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። በተለያዩ ጉዳዮች...