የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። ሚኒስቴሩ አልፎ አልፎ የአየር ክልሎች ሊዘጉና የጉዞ መስተጓጎል ሊያጋጥም እንደሚችል በመጠቆም፤ በውጭ ሀገር የሚገኙ አሜሪካውያን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የዩኤስ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ የሚወጡ የደህንነት መመሪያዎችን እንዲከተሉ አሳስቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፦ “ሚኒስቴሩ በዓለም ዙሪያ፣ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራል። በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ የሚወጡ የደህንነት ማስጠንቀቂያዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የአየር ክልል መዘጋቶች የጉዞ መስተጓጎል ሊያስከትሉ ይችላሉ” ብሏል።
መግለጫው አክሎም ከመካከለኛው ምስራቅ ውጭ ያሉ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት ኢላማ ሊደረጉ እንደሚችሉና #ኢራንን የሚደግፉ ቡድኖች በዓለም ዙሪያ ያሉ የአሜሪካ ጥቅሞችን ወይም ከአሜሪካውያን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ስፍራዎች ጥቃት ሊሰነዝሩባቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
ይህ የጉዞ ማስጠንቀቂያ የወጣው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት ጦርነቱ በቅርቡ ላይቆም እንደሚችል ፍንጭ ከሰጡ በኋላ ነው። ሚኒስትሩ በኤንቢሲ (NBC) ላይ ቀርበው እንደተናገሩት፤ አሜሪካ ይህንን ጦርነት በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል በቂ ሀብት አላት። “አንዳንዴ ውጥረትን ለማርገብ ሲባል ሁኔታዎችን ማባባስ ያስፈልጋል” ሲሉም ቤሰንት ተናግረዋል።
ከዕለቱ ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኢራን መሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጡ ሲሆን፤ በ48 ሰዓታት ውስጥ #የሆርሙዝ_ስርጥን ካልከፈቱ የአሜሪካ ጦር በኢራን የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከትልቁ ጀምሮ ሁሉንም እንደሚያወድም አስታውቀዋል።
እሁድ ማለዳ ላይ የኢራን ወታደራዊ ዕዝ ቃል አቀባይ አሜሪካ በነዳጅ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ካደረሰች ኢራንም በተመሳሳይ እርምጃ እንደምትመልስ አስጠንቅቀዋል። ኮሎኔል ኢብራሂም ዞልፋቃሪ ለኢራን መንግስታዊ የዜና ወኪል (IRNA) እንደገለጹት፤ “የኢራን የነዳጅ እና የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ጥቃት ከተሰነዘረባቸው፣ አሜሪካ እና በክልሉ ያለው አጋር አገዛዝ የሚጠቀሙባቸው የነዳጅ፣ የኢነርጂ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የጨው ውሃ ማጣሪያ መሰረተ ልማቶች ይመታሉ” ብለዋል።
