አይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ጠቅላላ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

Date:

የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ከግንቦት 12 እስከ 15 የሚቆየው ጠቅላላ ጉባኤው በአህጉሪቱ አካታች የዲጂታል ማንነት ሥርዓቶችን ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተነግሯል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ሀገራት መካከል የዕውቀት መጋራትን ትብብርን እና ፈጠራን በማጎልበት ህዝቦቿ ሕጋዊ ማንነት እና ጥሩ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በቅርብ ዓመታት ውስጥ ዲጂታል ማንነት ተስፋ ሰጪ ከሆነው ፈጠራ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረታዊ ምሶሶ ተሻሽሏል” ብለዋል።

“ዲጂታል ማንነት ከአሁን በኋላ አማራጭ ሳይሆን ሰዎችን ከአገልግሎቶች ከማኅበረሰቦች ከተቋማት እና ከመንግሥታት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ መሠረተ ልማት ነው” ሲሉም ጉባኤው ከከፈቱ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት ጽሑፍ አመላክተዋል፡፡

“ከአምስት ዓመት በፊት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ራዕይ እየተመራን እጅግ አስፈላጊ ውሳኔ ወስነናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህም ዘመናዊ አካታች መሠረት ያለው እና ሊሰፋ የሚችል ዲጂታል የማንነት ሥርዓት መገንባት መሆኑን አክለዋል።

“ዲጂታል የማንነት ሥርዓትን ለእያንዳንዱ ነዋሪ ተደራሽ የማድረግን ሥራ ‘ፋይዳ’ ብለን እንጠራዋለን” ያሉም ሲሆን ፋይዳ ካርድ ብቻ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ይልቁንም የግለሰቦችን ግላዊ መረጃዎች ምሥጢራዊነት በመጠበቅ እና አስፈላጊ የሆነውን ብቻ በማጋራት ማንነትን የሚያረጋግጥ ልዩ መለያ ቁጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ለፋይዳ እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የገለጹም ሲሆን 90 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ሆኑንም አንስተዋል፡፡

እንደ ፋይናንስ፣ ጤና እና ትምህርት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች የተቀናጀው ፋይዳ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ባለስልጣናት፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

(አሐዱ ሬድዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...