ጉባዔው ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ አሠራሮችን በማሻሻል የነጋዴውን እንግልት ይቀርፋል ተብሏል።
የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ የመማክርት ጉባዔውን በሰብሳቢነት ይመሩታል።
(አዲስ ቻምበር ጥቅምት 15:2018) የአዲስ አበባ ገቢዎቸ ቢሮ በየአመቱ በመቶ ቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በግብር መልክ ይሰበስባል፡፡
ከዚህ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት ውስጥ ወደ 90 መቶ የሚሆነው ግብር የሚመነጭው ከአዲስ አበባ ነጋዴዎች ነው፡፡
ይሁን እንጂ በግብር አሰባሰብ ወቅትም ሆነ በአሠራር ስርአት ከንግዱ ህብረተሰብ ቅሬታዎች ሲነሱ ይስተዋላል ።
የአዲስ አበባ የገቢዎች ቢሮም ቅሬታዎችን አቅም በፈቀደ መጠን ምላሾችን እየሰጠ እንደሆነ የገለፀ ቢሆንም ቅሬታዎችና የአሠራር ማስተካከያዎች በተደራጀ መልኩ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በኩል ቢቀርቡ ትልቅ ውጤት እንደሚገኝ ሲገልፅ ቆይቷል።
የአዲስ ቻምበር አመራሮች በተገኙበት እና በዛሬው እለት የተመሠረተው የመማክርት ጉባዔ አንጋፋውን የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት በሰብሳቢነት በሙሉ ድምጽ መርጧል፡፡
50 መቀመጫዎች ያሉት ይኽው ጉባዔ 7 የሥራ አስፈጻሚ እና የተለያዩ ኮሚቴዎች እንዳሉት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተመልክቷል፡፡
ጉባዔው የቢሮውን የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ይፈትሻል፤ ለብልሹ አሠራሮች በር የሚከፍቱ አሰራሮች እንዲሻሻሉ ፤ የተገልጋዮችን ቅሬታ ይቀበላል፤ ይመረምራል፤ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አግልግሎት ሥርዓት እንዲረጋገጥ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በአገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት ዘንድ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ የአስራር ሪፎርም ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ በየተቋማቱ በዋናነት የተገልጋዩን ሕ/ሰብ እና ሌሎች ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት የመማክርት ጉባዔያት በማቋቋም በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ የግልጽነት እና ጠያቂነት ባሕል ለማረጋገጥ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የገቢዎች ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መሐመድ አብዱራሕማን ለጉባዔተኛው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቀልጣፋ፤ግልጽና ተጠያቂነትን የሚያረጋገጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ ለማደረግ በሁሉም ክ/ከተሞችና ወረዳዎችና ተመሳሳይ የመማክርት ጉባዔያት መቋቋማቸውን ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ መሐመድ አብዱራሕማን አስታውሰው ከሌብነትንና ብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ በ 88 ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡፡
የመማከርት ጉባዔው በራሱ በነጋዴው ነጻ ማህበር ማለትም በአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ እንዲመራ መደረጉ ወደ 450 ሺሕ ለሚጠጉ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች መልካም ዜና እንደሆነ የጉባዔው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የመማክርት ጉባዔው የሥራ ዘመን 2 አመት ሲሆን ለ1ተጨማሪ አመት ሊራዘም እንደሚችል ለመረዳት ተችሏል፡፡
