ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሳይበር ጥቃት ምክንያት የምታጣው የገንዘብ መጠን ከ10 ትሪሊየን ብር ሊሻገር እንደሚችል ተገለጸ።
ይህ መግለጫ የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (CBE) የሳይበር ደኅንነት ወርን አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና የመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ ወቅት ነው።
ባንኩ እንዳስታወቀው፣ የፋይናንስ ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከጥንቃቄ ጉድለት እና ከተያያዥነት ካላቸው ጉዳዮች የመነጨ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የሳይበር ደኅንነት ወር በአገር አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ እየተከበረ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ባንኩም ለሁለተኛ ጊዜ የሳይበር ደኅንነትን እና በኢኮኖሚ ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና በሚመለከት ሰፊ ገለጻ ማቅረብ ችሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረገው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ሰዓት በቀን ውስጥ 2,200 የሳይበር ጥቃቶች እንደሚፈጸሙና በቀን ውስጥ 75 የሚሆኑ ከባድ የጥቃት ሙከራዎች እንደሚደረጉ አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በሳይበር ጥቃት 10 ትሪሊየን ብር የሚሆነውን የገንዘብ መጠን በየዓመቱ እንደምታጣ ገልጿል።
በመድረኩ ላይ እንደተነሳው፣ የዘመኑ የሳይበር ጥቃቶች ከወትሮው የተለየ ውስብስብነት አላቸው። በመሆኑም፣ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ሙሉ ለሙሉ አዲስ የሥራ ሂደት መከተል ተገቢ መሆኑ ተመላክቷል።
ባንኩ የዲጂታል ስትራቴጂዎችን መከተል በመቻሉ ከ90 በመቶ በላይ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ ሲሆን፣ ይህም ባለፉት ጊዜያት ከነበረው የተጠቃሚ ቁጥር 17 በመቶ በላይ አብላጫ ቁጥር ማስመዝገብ እንደቻለ አመላክቷል። በባንኩ ዘርፍ የሚገጥሙ የሳይበር ጥቃቶችን ለመፍታት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (Artificial Intelligence) መጠቀም የግድ በመሆኑ፣ ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ስራዎች እንደሚሰሩ ባንኩ አስታውቋል።
ከሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 56 በመቶ ያህሉ በሰርጎ ገቦች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው ተብሏል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታጣው የ10 ትሪሊየን ብር ገንዘብ ወደ 13 ትሪሊየን ብር የማሻቀብ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የዲጂታል ስትራቴጂው እየፈጠነ መሄድ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን እያባባሰ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይ ኢትዮጵያን በሳይበር ጥቃት የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ሊያደርጋት እንደሚችል ስጋት ተገልጿል።
(መናኸሪያ ሬዲዮ)
