በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስቲያኖች፣ ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸርካ ወረዳ 3 ክርስቲያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስቲያኖች በድምሩ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ብቻ 25 ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉና ግድያውም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የላከውን ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ የተመለከተው በከባድና ጥልቅ የኃዘን ስሜት ነው ፡፡
በመሆኑም በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት እንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም የቆየው በተደጋጋሚ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ በነጻነት የማምለክ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ፣ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ክብረ ነክና ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጽኑ አውግዞታል፡፡
በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በጽኑ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የእምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩልንና ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ሕገ ወጥ ግለሰቦች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪም በቀጣይ እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይደገም ፤አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቋሚ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
በመጨረሻም በደረሰው ጉዳት የተሰማንን ከፍተኛ ኃዘን በድጋሚ እየገለጽን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን በመመኘት በግፍ ሕይወታቸውን ወገኖቻችንም ላጡት እግዚአብሐር አምላክ ዕረፍተ ነፍስን እንዲያድልልን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ
ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
