በቴፒ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል አንዲት እናት በ28 ሳምንት የእርግዝና ቆይታ ከ1 ኪሎ ግራም በታች የሚመዝን ህፃን በሰላም ተገላግላለች።
ህፃኑ ሲወለድ ክብደቱ 895 ግራም ብቻ ይመዝን የነበረ በመሆኑ በሆስፒታሉ የቅርብ ክትትል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን በሆስፒታሉ የህፃናት እስፔሻሊስት ዶ/ር አብርሃም ሞላ በተለይ ለኢቢሲ ገልፀዋል።
የአንድ ጤነኛ ህፃን በእናቱ መሀፀን ውስጥ የሚኖረው የቆይታ ጊዜ ከ37 ሳምንታት እስከ 40 ሳምንታት ሲሆን ህጻኑ ሲወለድ ክብደቱ ዝቅተኛ ነው የሚባለው ደግሞ ከ2.5 ኪ.ግ በታች የሚመዝን ሲሆን እንደሆነ የጤና ባለሞያዎች ይገልፃሉ።
እናትና ልጁ በቴፒ አጠቃላይ ሆስፒታል ከ23 ቀናት የህክምና ክትትል በኋላ በሠላም ወደ ቤታቸው መሄዳቸውንም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት በ28 ሳምንት እድሜና ከአንድ ኪሎ ግራም በታች ከሚወለዱ ህጻናት በህይወት የመቆየት እድላቸው እስከ 40 በመቶ ብቻ መሆኑንም ባለሞያው ጠቁመዋል።
ያለጊዜያቸው ቀድመው የሚወለዱ ህጻናት ብዙውን ጊዜ በእናታቸው መሀፀን ውስጥ ወሳኝ የሆነውን የእድገት ሂደት በሙሉ ወይም በከፊል ስለማያጠናቅቁ ቅርብ የሆነ የሕክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል።
እንደ ዶ/ር አብርሃም ገለፃ በሆስፒታሉ የሚገኙ ባለሞያዎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ የህጻኑን ህይወት በተሳካ ሁኔታ ለመታደግ ተችሏል።
ሆስፒታሉ ለእናቶችንና ሕፃናት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስዘመን ተገቢ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
ebc
