8 ሺህ 613 የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ላይ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የዲሲፕሊን ርምጃ መወሰዱን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።
በፓርቲው የተወሰደው ርምጃ ከኃላፊነት ማንሳት፣ ከደረጃ ዝቅ ማድረግ እና ሽግሽግን ያካተተ መሆኑን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ቃል የገባዉን በተግባር እንዲያረጋግጥ በየደረጃው ያለዉ አመራር እና አባል በጥሩ ስነ-ምግባር ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
በቀጣይ የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ በማይወጣ፣ ሕዝቡን በታማኝነት የማያገለግል፣ በብልሹ አሰራርና ሌብነት ውስጥ የተዘፈቀ አመራር ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል ተብሏል።
በየደረጃው ያለዉ አመራር እና አባል በጥሩ ስነ ምግባር ኃላፊነቱን እንዲወጣ በዚህም የህዝብ ተጠቃሚነት እና ኑሮ እንዲሻሻል ስርዓት እንዲገነባ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አደም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ነጻ ሆኖ በህዝብ ታማኝነት ያለው ሆኖ እንዲካሄድና እንዲጠናቀቅ ፓርቲው የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን አቶ አደም ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 14፣ 2018 ስብሰባ አካሄዷል።
