የየመን ሑቲ አማፂ ለ5 ዓመታት በእስር ላይ ያቆያት የመኒ-ኢትዮጵያዊት ሞዴል እንቲሳር አል-ሐማዲን መለቀቋን ጠበቃዋና የፀጥታ ምንጮች መናገራቸውን የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገበ።
ከኢትዮጵያዊት እናትና ከየመናዊ አባት የተወለደችው የ23 ዓመቷ እንቲሳር አል-ሐማዲ፣ በየካቲት 2013 ዓ.ም በሰነዓ ከተማ ለፎቶ ቀረጻ እየሄደች ሳለ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለችው።
ሞዴሏ በወቅቱ፣ “አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀምና ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት በመፈጸም” ወንጀል ክስ ቀርቦባት ለአምስት ዓመታት ማረሚያ ቤት እንድትወርድ የተፈረደባት ሲሆን፤ በጠበቃዋና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ክሶቹ ሀሰት መሆናቸውንና በሴቶች ነጻነት ላይ የተቃጣ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።
ጠበቃዋ ካሊድ አል-ከማል፤ “እንቲሳር አል-ሐማዲ ትናንት ምሽት ከእስር ተለቃ ቤቷ ገብታለች” ሲል ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግሯል። አክሎም፤ “እንቲሳር በተለያዩ በሽታዎች ስትሰቃይ የነበረ ሲሆን፣ የደረሰባት ኢ-ፍትሃዊነትም የነበረችበትን ሁኔታ አባብሶት ነበር።” ብሏል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንቲሳር በ2013 ዓ.ም. ራሷን የማጥፋት ሙከራ አድርጋ እንደነበር በወቅቱ መግለጻቸውንም ጠበቃዋ አስታውሷል።
