የኩክየለሽ ማርያም ገዳምና ሌሎች ሦስት ቤተ መቅደሶች በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የህልውና ስጋት የተጋረጠባቸው በመሆኑ፤ ሁሉም ይመለከተኛል የሚል አካል አስቸኳይ እርብርብ እንዲያደርግ ገዳሙ ጠይቋል።
ኩክየለሽ ማርያም ገዳም ከደብረ ብርሃን ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ሲሆን፤ ቤተ መቅደሱን ከአለት የመፈልፈል ተግባር 1972 ዓ.ም. ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም. ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተጀምሯል።
ገዳሙን የፈለፈሉት አባ ሃይለ ጊዮርጊስ የተባሉት ጻድቅ በተወለዱ በ64 ዓመታቸው፤ ኩክ የለሽ ማርያምን ጨምሮ 4 ቤተ መቅደሶች እና ከ50 በላይ የባህታዊያን መኖሪያዎችን ፈልፍለዋል።
ከዚያ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ገዳሙ በማቅናት ከተለያዩ በሽታዎች መፈወሳቸውን ከዓይን እማኞች በተጨማሪ በምስል የተደገፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከፍልፍል ቤተ-መቅደሶቹ መካከል በገዳሙ ግርጌ የሚገኘው የኩክ የለሽ ማርያም በተፈጥሮ አደጋ የተነሳ የመደርመስ ስጋት መደቀኑን የገዳሙ አስተዳዳሪ መላከ ምህረት ቆሞስ አባ ሙሴ መካሻ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በገዳሙ ከሚገኙት አራት ቤተ መቅደሶች መካከል አንዱ የሆነው የምንያምር ገብርኤል ቤተ መቅደስ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የመደርመስ ስጋት የተደቀነበት ሆኗል። ገዳሙን ለስጋት ከዳረገው መካከል አንዱ በእፅዋት ስሮች የቤተ መቅደሱ ጣሪያና ግርግዳዎችን መሰነጣጠቅ ይገኝበታል።
ከአሁን ቀደም ፍሳሽ ወደ ውስጥ በማስገባት አገልግሎት እስከ ማስታጎል የደረሰ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት የገዳሙ አስተዳዳሪ፤ መጪው ክረምት ከመግባቱ በፊት እልባት ካልተሰጠው የመደርመስ ስጋት መደቀኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከአሁን ቀደም በመቅደሱ አቅራቢያ የመደርመስ አደጋ መከሰቱን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፤ ገዳሙን ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ ሁሉም ይመለከተኛ የሚል አካል አስቸኳይ እርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአፄ ዘርዓያዕቆብ የባህል ታሪክና ቋንቋ ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዘመነወርቅ ዩሃንስ በበኩላቸው፤ ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ገዳሙን ተዘዋውሮ መመልከቱን ተናግረዋል።
የባለሙያዎች ቡድን ገዳሙ ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ ጥናት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቅርቡ ምን ያክል ገንዘብ ያስፈልጋል የሚለውን ጨምሮ የጥናቱ ውጤት ይፋ ይደረጋል ያሉት የገዳሙ አባቶች፤ ገዳሙ ቅርስ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለይም የ2017 ዓ.ም. ክረምት ከመግባቱ በፊት ሥራዎች ካልተሰሩ የሚደርሰው አደጋ ገዳሙ ሙሉ በሙሉ እስከመናድ የሚደርስ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ተመላክቷል።
የገዳሙ የድጋፍ ማሰባሰቢያ አካውንት ቁጥር
ሣሪያ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል እና አንቀፀ አድኅኖ ቅድሥት ኩክለሽ ማርያም ገዳም
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
1000684624966
አባይ ባንክ
381111051638114
ለተጨማሪ መረጃዎች
+251 92 727 5247
+251 97 311 1281
+251 97 311 1281
በአበረ ስሜነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
