የሁለት ዓለም ስንብት

Date:

ከዕዝራ እጅጉ


ግዮን መጽሔት :- ቀዝቃዛው የሰኔ አየር …….  ቸርነት…. በመገናኛ አደባባይ ላይ ቆሟል። ዙሪያውን የሚተላለፈው ሕዝብእንደ ወንዝ ይፈሳል፤ እርሱ ግን ደርቆ ቀርቷል። እግሩ ሥር፣ አቧራ የለበሰ አስፋልት ላይ አንዲት እናት ተቀምጣለች። ሦስት ልጆችበዙሪያዋ ታቅፈዋል። ከፊቷ የዘረጋችው በላስቲክ የተሸፈነ ወረቀት ግን እንደ ጩቤ ልቡን ወጋው።

በወረቀቱ ላይ ያለው ፊርማ የራሱ ነው…. የቸርነት ኃይሉ!

ከሦስት ወር በፊት በቢሮው ወንበር ላይ ተቀምጦ በቸልታ ያሰፈረው ፊርማ፣ ዛሬ ጎዳናላይ ለልመና ምስክር ሆኖ ቆሟል። የልጆቹ ዐይን ውስጥ ያለው ባዶነት፣ በዚያች ቀን የፈረደው አንድ ሰው ላይ ብቻ እንዳልነበረ ገባው።የከተማዋ ጫጫታ እየራቀው ሄደና ትውስታው ሦስት ወር ወደኋላ ተመለሰ…

***

ገና በጧቱ ቢሮ ለመግባት ሲወጥን ድካም ተጫጫነው። ትናንት ያመሸበት ሠርግ ክፉኛጎድቶታል። መጠጡ፣ ጭፈራው፣ ምግቡ ተደማምረው አልጋው ላይ እንዲውል ይሞግቱታል። ወዲህ ደግሞ የስድስት ወር ሪፖርት የሚቀርብበትቀን ስለሆነ ቢሮ መገኘቱ የግድ ነው። በሁለት ልብ ውስጥ ሆኖ ከአልጋው ተነሳ።

የሥራ መሪ መሆን የሰለቸው ይመስላል። አለቃ ሆነ የበታች ሁሉም ያው ተቀጣሪ ነው።በሥራ አስኪያጅነት መሾም ጥቅማ ጥቅሙ ቢበዛም ነፃነትን ግን ይጋፋል። በዚያ ላይ ከታች ያለው ክፉ አለቃ ሲያደርገው አለቆቹ ደግሞመወሰን የማይችልና አቋም የሌለው አድርገው ይስሉታል። የገና ዳቦ መሆን ነው ትርፉ ይላል፡፡ ከላይም ከታችም እሳት፡፡

ቸርነት ኃይሉ እህል ውሃም ሳይቀምስ 200 ሰዎችን ወደ ሚመራበት መስሪያ ቤቱ ለማቅናት  መኪናውን አስነሳ። መኪናውንም ከነ ቤንዚኑ የሚኖርበትንም ቤት ከነሙሉ ዕቃውያገኘው በመሾሙ ነው። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ በዚሁ መስሪያ ቤት 23 ዓመት ሲያገለግል አንድም ቀን ዐይኑ ወደ ሌላ መስሪያቤት አማትሮ አያውቅም። አሁን በ45 ዓመቱ ግን መሰላቸትና የሥራ ፍላጎት ማጣት ተጣምረው መንፈሱን እየገዘገዙት እንደሆነ ይሰማዋል።ቸርነት መኪና ውስጥ ሆኖ ስለ ሥራው እያሰበ  ድንገት የፅሑፍ መልዕክትሞባይሉ ላይ መግባቱን ተረዳና ማንበብ ቀጠለ።

‹‹…ሰላም አደሩ አለቃ!!!…….. ባጠፋ እንኳን እንዲህ በጥድፊያ ያለአንዳች ማስጠንቀቂያ ከሥራ ትሰናበታለህ ብለው አለቆቼ የነገሩኝ ፍትሐዊ አይመስለኝም። እርግጥ ደብዳቤው አልደረሰኝም። ነገር ግንየመጨረሻው ውሳኔ በእርስዎ የሚፀና ነውና ጭንቅ ቢለኝ ይህን መልዕክት ላኩልዎት። ነገሩን በጥሞና አይተው እንዲወስኑ እንጂ እንዲጨናነቁአልፈልግም። ጠዋት ቢሮዎ የመጣሁ አሁንም አለው። መልካሙን ሁሉ እመኛልዎታለሁ›› ይላል፡፡

ጽሑፉ የታዲዮስ በላይነህ ነው፡፡

የጽሑፉን መልዕክት ካነበበሚል በኋላ ይበልጥ ተረበሸ። በሰው እንጀራ መወሰን፣ ሰው ይባረርአይባረር በሚለው ላይ ፊርማን ማሳረፍ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ አሰበ። ይህ ሰው በቀጣይነት ደሞዝ ይኑረው አይኑረው የሚወሰነው በሥራአስኪያጁ ነው። የሥራ መሪ ሆኖ በቆየባቸው 9 ዓመታት እነዚህን በመሰሉ ፈተናዎች ቁጭ ብድግ ብሏል።

ጥፋት ከሆነ ደግሞ የግድ መወሰን አለበት። ጥፋተኛ ካልተቀጣ፣ መሰናበት ያለበት ካልተሰናበተ፣መርህ አይከበርም። ሰራተኞች ለመስሪያ ቤት ደንብ ካልተገዙ ሁሉም በረት ውስጥ እንዳለ ከብት እንዳሻው ይሆናል። ቸርነት ይህን እያሰበደግሞ በሌላ በኩል ሰዎች ከሥራ ቢሰናበቱ የሚገጥማቸው የኑሮ ችግር ይታሰበዋል። ሥራ አስኪያጅነቱ ቢቀርብኝስ ብሎ እንዲያስብ የሚገፋፋውም ይሄው ነው።

ሙያውን ቢወደውም መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለውን መቆሚያ የሌለውን መጠላለፍ ከተፀየፈው ሰነባብቷል። እሱን ጠልፈው ጥለውየእሱን ቦታ ለመያዝ የቋመጡ አንድ ሁለት ሰዎች እንደ ሰጎን እንዳደፈጡ ካወቀ ሰንብቷል። ተንኮል በሰፈነበት መስሪያ ቤት ውስጥመሪ መሆን ፈተና ነው ሲል ቸርነት አሰበ። ይህን እያሰበም መስሪያ ቤቱ ደረሰ። ገና ደረጃውን መውጣት ከመጀመሩ ውጥረቱ ባሰበት።የመጠላለፉ ድራማ ማብቂያው መቼ እንደሆነ ናፍቆታል። ከስሩ ያሉት የውሸት ሳቅ እየሳቁ ጉድጓድ ይምሱለታል። እርሱም ቦታውን ላለመልቀቅእንደ አቅሚቲ ይታትራል።

‹‹ሰላም አደርሽ ናርዶስ›› በማለት ቸርነት ለፀሐፊው ሰላምታ ሰጥቶ ቢሮውን ከፍቶገባ። ገና ከመግባቱ ናርዶስ ተከተለችው፡፡ገብቶታል፡፡

‹‹….አቶ ቸርነት ያ አስተዳደር ክፍ
ል የሚሠራው ሰውዬ ከመጣ ቆይቷል። ታዲዮስንያውቁት የለ!!! የግድ እርሳቸውን የማነጋግርበት ጉዳይ አለኝ ብሏል። ላስገባው›› ስትል ናርዶስ ፍቃድ ጠየቀች።

ሳያመነታ ‹‹አስገቢው›› አላት።

ታዲዮስም ፊቱ በደስታ ተሞልቶ ገባ።

‹‹የ
ማነጋገር ዕድሉን ስላልነፈጉኝ አመሠግናለሁ አቶ ቸርነት። ብዙ ጊዜ በራቸውንክፍት አድርገው ሀሣብ ለመስማት ትዕግሥት ያላቸው አለቆች ይመስጡኛል›› በማለት ታዲዮስ አድናቆት በመቸር ወደ ጉዳዩ ለመግባት ተንደረደረ።

ቸርነትም ትኩር ብሎ ካየው በኋላ፤

‹‹በሞባይል የላከውን አይቼዋለሁ። ነገሩን ከሥሩ ማጥራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።እኛ እዚህ ያለነው የመስሪያ ቤቱን ሕግና መመሪያ ለማስከበር ነው። ደሞዝ የሚከፈለንም ለምንወስናቸው ጥሩ ውሳኔዎች ነው። ሕግ የማይከበርከሆነ መስሪያ ቤት ነፍስ አይኖረውም። እናም ያንተ ጉዳይ ምን እንደሆነ በዝርዝር ባላውቅም ዞሮ ዞሮ ብቻዬን የምወስነው ነገር ባይሆኖምአንተ የምትለውን ለማዳመጥ ግን ዝግጁ ነኝ›› በማለት ቸርነት ተናገረ።

‹‹አቶ ቸርነት ሀሣቤን እንድሰጥ ዕድል ስላልነፈጉኝ ምስጋናዬ ጥልቅ ነው። እኔ እዚህመስሪያ ቤት ከ10 ዓመት በላይ ሰርቻለሁ። በሥራዬ መካከለኛ አፈፃፀም አለኝ። ስለራሴ ማውራት አይሁንብኝና ሥራዬን እወዳለሁ ፤አከብራለሁ፡፡ ያው እንደሚያውቁት ደሞዜ ወር አያደርሰኝም። በመሆኑም ተባራሪ ሥራዎች ማለትም ልጆችን የማስጠናት፣ በትርፍ ሰዓትፎቶ የማንሳት ሥራንም እየሠራሁ ኑሮዬን ለመደጎም እየታገልኩ ነው።

ጥፋት ሆኖ የተገኘብኝም በትርፍ ሰዓት መስራቴ ነው። በእርግጥከሥራ ሰዓቴ ውጭ የሠራሁት በመሆኑ መስሪያ ቤቱን አልበደልኩም። እንዲያውም አሁን የውጭ ሥራው ቀዝቅዞ ያቺው ደሞዜ ናት የምታኖረኝ።አለቆቼ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ መሰናበትህ ስለማይቀር ራስህን ብታዘጋጅ ይበጃል እያሉኝ ነው። መፍትሔ ሳጣ ወደ እርስዎ መጣሁ።››ሲል ታዲዮስ የውስጡን ተነፈሰ።

ሥራ አስኪያጁ ቸርነት ለደቂቃዎች ካሰበ በኋላ

‹‹ስንት ነው ደሞዝህ?›› ሲል ጠየቀው፤

‹‹12,000 ብር ነው›› ሲል መለሰ።

‹‹እርግጥ ነው በ12,000 ብር ደሞዝ መኖር ፈታኝ መሆኑ
ን እገነዘባለሁ። ነገርግን አለቆችህ ቅሬታ ያነሱብህ ለምን ይመስልሃል? ምናልባት ከሥራ ገበታህ ላይ ሳትገኝ ሥራ በድለህ ከሆነስ? አሊያ ደግሞ አለቃህያዘዘህን ሳትፈፅም ቀርተህ ቢሆንስ?›› አለና ቸርነት በረጅሙ ተነፈሰ።

‹‹….አለቃ እኔ ሥራዬን እወደዋለሁ። ከአለቆቼ ጋር ግን
አልፎ አልፎ በሐሣብናበንግግር መጋጨቴ አልቀርም። ያው አብሮ የሚሠራ ሰው የሐሣብ ፍልሚያ ሊገጥም ይችላል። እኔም ፍፁም ነኝ ብዬ ልመፃደቅ አልችልም።ይሁንና 10 ዓመት ከሰራሁበት ቤት በዚህ ሁኔታ መሰናበት ያለብኝ አይመስለኝም። አለቆቼ ቢጠየቁ ሌላ ነገር እንደሚያስረዱ አውቃለሁ።እርስዎ ግን ግራና ቀኙን አይተው ሊፈርዱ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት በማሳደሬ ነው ቢሮዎ የመጣሁት።›› አለ ታዲዮስ ሥራ አስኪያጁንበልምምጥ እየተመለከተ።

ቸርነት በውስጡ ብዙ ሐሣቦች ተራወጡበት። ነገሩን ከሥር ከመሠረቱ ማጣራት እንዳለበት አሰበ። የተንኮል ድር በደራበት ቤት እንዴት ፍትሕ ማግኘት እንደሚቻል ቆም ብሎ አሰበ።

‹‹አቶ ቸርነት ይህች በምስሉ ላይ የሚያይዋት ባለቤቴነች። የቤት እመቤት ስትሆን የሦስት ልጆቼም እናት ነች። እነዚህ ደግሞ ልጆቼ ናቸው። ትልቁ 11 ዓመቱ ሲሆን ተከታዩ 8 ነው። ትንሿ አራት ዓመቷ ነው›› ሲልታዲዮስ ቦርሳው ውስጥ የነበረውን የቤተሰቡን ፎቶ ለአለቃው አሳየ።

ቸርነት የበለጠ ተረበሸ። ፎቶውን በእጁ ይዞ እየተመለከተ የራሱን ልጅነት አስታወሰ።አባቱ ምን ያህል ተቸግሮ እንዳሳደገው ፈፅሞ ሊዘነጋው አይችልም።

‹‹…ታዲዮስ እኔ ማንም ሰው ተቸግሮ ኑሮን እንዲገፋ አልፈልግም። የሰው ልጅ በብዙፈተና ያልፋል። ሁላችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለፍነው። የአንተን ጉዳይ በተመለከተ ግን ከአለቆችህ ጋር ስብሰባ ተቀምጠን እናየዋለን።እኔ በበኩሌ የመስሪያ ቤቱን መመሪያ እና ደንብ ብሎም ከአለቆችህ የማገኘውን ሪፖርት መሠረት አድርጌ እወስናለሁ።›› በማለት አቶ ቸርነት መልስ ሰጠ።

ተስፋ የሰነቀው ታዲዮስም፣ አለቃውን አመስግኖ ቢሮውን ለቆ ወጣ።

‹‹ይህች ዓለም ፈታኝ ነች›› አለ ሥራ አስኪያጁ ቸርነት። ታዲዮስ በሩን ዘግቶ ከወጣ በኋላ ቸርነት ጭንቀቱ በረታ። ለአፍታም ሳይቆይ የስልክ መነጋገሪውን አንስቶ ፀሐፊውን ጠራት። በታዲዮስ ጉዳይ ውሳኔ ለመወሰን የክፍልኃላፊዎችን እንድትጠራ ነግሯት ለምሳ ከቢሮ ወጣ።

***

በታዲዮስ ጉዳይ ለመወሰን 6 የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጠረጴዛ ከበው ስብሰባ ይዘዋል ።


‹‹እኔ በተራ ምክንያት የቤተሰብ ኃላፊ እንጀራውን እንዲያጣ አልፈልግም›› ይላል አንደኛው፡፡

‹‹ይህ መመሪያ የማስከበር ጉዳይ ነው። ማንም እንጀራውን እንዲያጣ የሚፈልግ የለም›› ይላል ረጅሙ አለቃ፡፡

‹‹ሁላችንም ሥራ ልንሠራ ነው የመጣነው። ለመስሪያ ቤቱ የሚጠቅም ውሳኔ እንወስን። ለሕሊናችንም ተገዢ እንሁን።›› ይላል አንደኛው ቆፍጣና የሥራ መሪ።

አንዱ ብቻ በራሱ ጉዳይ በሐሣብ ጭልጥ ብሏል። ምን አስተያየት እንዳለው እንኳን አይታወቅም።

አለቃ ቸርነት በእንዲህ ዓይነት የቢሮ መጠላለፍ ውስጥ ቢያልፍም ሂደቱ እያሰለቸውመጥቷል። ማንም ለማንም እንደማይተኛ ያውቃል። ስለ ታዲዮስ መልካም ነገር ቢያወራ ሰበብ ፈጥረው የሚመራቸው ባልደረቦቹ ጉድጓድ ይምሱለታል።

‹እነዚህ እርኩሶች ለእኔም አይመለሱ› ሲል አሰበ። አንድ ጊዜ ፊታቸውን ሌላ ጊዜደግሞ የሰውነታቸውን መቁነጥነጥ ሲመለከት የሆነ ሤራ እንዳለ ተገነዘበ። ግን የምን ሤራ? የተጨበጠ መረጃ  የለውም። ሥራ አስኪያጅነቱን የሚጠላው እዚህ ጋር ነው። ለሰው መራራትና የውሳኔሰው መሆን የሚሉት ሐሣቦች አጣብቂኝ ውስጥ ይከቱታል።

ስብሰባው 3 ሰዓት ፈጀ። አንድ ሰው ይባረር አይባረር በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት180 ደቂቃዎች ነጎዱ። አንደኛው ስብሰባው ሰውነቱን ሲያደክመው ሌላኛው ደግሞ የተንኮል ወይም የመጠላለፍ አባት ስለሆነ እየተነቃቃተጨማሪ 180 ደቂቃ ቢጨመርም ግድ የለውም። ከሥራ አስኪያጁ በቀር ሁሉም በአንድ ድምፅ ታዲዮስ ላይ እንዲሰናበት ወሰኑበት። አንዳንዱምምን እንደወሰነ ሳይገባው በሰው እንጀራ ላይ ድምፅ ሰጥቷል።

‹‹እንግዲህ አለቃ እኛ ከመሥሪያ ቤቱ ደንብ አንፃር ወስነናል። የመጨረሻ ውሳኔ ያንተነው፤ አሉን የምንላቸው ማስረጃዎች በቃለ ጉባኤ የተያዙ በመሆኑ ለውሳኔ የሚቸግርህ አይመስለኝም›› አለ አንደኛው የሥራ መሪ። አምስቱምብድግ ብለው ተነሱና ተከታትለው የሥራ አስኪያጁን ቢሮ ለቀቁ።

ሥራ አስኪያጁ ከወጡ በኋላ ‹ከእነዚህ ሰይጣኖች ጋር ነበር የምሠራው› ሲል በሆዱአወራ። ከልቡ ጠላቸው። ቢሆንም ግን ለእርሱ የማይተኙ፣ ጉድጓድ የሚምሱለት ክፉዎች ስለሆኑ አጣብቂኝ ውስጥ ቢከቱትም መወሰን እንዳለበትግን ተረዳ።

እነርሱ ከወጡ በኋላ ቃለ ጉባኤውን ያነብ ገባ። በአእምሮው ብዙ ጉዳዮች ተመላለሱ።‹ቸርነት እስከ መቼ ቸር ትሆናለህ?› ራሱን ጠየቀ። ብዙ ካወጣ ካወረደ በኋላ የስንብት ደብዳቤው እንዲጻፍ ወሰነ።  ፀሐፊውንም ጠርቶ ደብዳቤው ተጽፎ ለታዲዮስ እንዲደርሰው አድርጊ አላት። እርሷምየተባለችውን አደረገች።

***

ከ3 ወራት በኋላ

ቸርነት የሚያየውን ነገር ማመን ተስኖት ጎዳና ላይ አላፊ አግዳሚው የሚያየውን ደብዳቤ አብሮ ያነብበው ጀመር።


‹‹አቶ ታዲዮስ በላይነህ በመሥሪያ ቤቱ ውሳኔ ከሥራ የተሰናበቱ ስለሆነ ይህንኑ ለአስተዳደርእና ፋይናንስ እናሳውቃለን ፤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቸርነት ኃይሉ›› ይላል፡፡

ሥራ አስኪያጁ ቸርነት የእግር ጉዞውን አቁሞና ቆም ብሎ አሰበ። ለምትለምነው እናት 600 ብር አውጥቶ ሰጠ። እርሷም ደንግጣ ተመለከተችው። እርሱም ዳግም መስሪያ ቤቱ አልተመለሰም።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር  233 ግንቦት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...