በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሳቢያ የማዳበሪያ ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን፤ ማዳበሪያን ወደሀገር ውስጥ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ለቀናት በቆሙ ቁጥር ወደብ ላይ ለሚቆይ አንድ መርከብ ኢትዮጵያ በቀን 23 ሺሕ ዶላር ለመክፈል እንደምትገደድ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ያለው መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ/ም በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።
ሚኒስቴሩ ፥ ” ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በአግባቡ እየተሰራጨ አይደለም ” ሲልም ገልጿል።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ፣ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቀድማ ብትገዛም የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በቀጣይም በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ” በጣም ከፍተኛ ” እንደሚሆን ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
” ለምሳሌ ከዛሬ 40 ቀን በፊት ዩሪያ ማዳበሪያ ለመግዛት ድርድር በምናደርግበት ጊዜ ማዳበሪያውን የሚያመርቱ ሀገራት አንዱን ቶን በ430 ዶላር እንድንወስድ ሲያቀርቡልን ነበር። ዛሬ ግን ትላንት የተደራደርናቸው ሀገራት በቶን ከ870 ዶላር ከእጥፍ በላይ ዋጋ ጨምረው የታየበት ሁኔታ አለ ” ብለዋል።
መሰል ቀውሶች በማግስቱ የሚያስከተሉት ” የምግብ ዋስትና ቀውስ ” እና ” የምግብ ሰንሰለት መዛነፍ ” መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ” እዛ ፈተና ሳንወድቅ ” የሚታረስን መሬት በአግባቡ ማረስ”፣ ” የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ” መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዘንድሮ የሚሆን ማዳበሪያ ቀድሞ መግባቱን አንስተው፣ ” መሰረታዊ ችግሩ ግን ማዳበሪያው ወደ ማዕከላዊ መጋዝኖች እና ዩኒየኖች ከደረሰ በኋላ ለአርሶአደሩ በአግባቡ እየተሰራጨ አይደለም ” ብለዋል።
” ያ አለመሰራጨት በየቀኑ የመኪኖችን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነው ” ብለው፣ ” ተሽከርካሪዎች ማዳበሪያ ጭነው 5 ቀን፣ 7 ቀን፣ 10 ቀን መጋዝኖች አካባቢ የሚቆሙበት ሁኔታ ነው ያለው። ያ ደግሞ ወደብ ላይ የሚቆሙ መርከቦችን ላለአስፈላጊ ቆይታ ያጋልጣቸዋል ” ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም፣ ” አንድ መርከብ ከተያዘለት ቀን ቀላይ ወደብ ላይ ከቆዬ ኢትዮጵያ ለአንድ መርከብ በቀን 23 ሺሕ ዶላር ትከፍላለች ” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ክልል ላይ ያሉ አካላት በሚፈለገው መጠን ትኩረት ባለመስጠት፣ ችግሩን ባለመረዳት ችግሩ አለመፈታቱን አስረድተዋል።
የግንዛቤ ክፍተቱን ሲያስረዱ፣ ” ማዳበሪያ ዝም ብሎ ይመጣል። መኪና ቢቆምም ባይቆምም ችግር የሌለው ነው የሚመስለው ” ነው ያሉት።
የጉዳቱን አስከፊነት ሲገልጹ ደግሞ፣ ” ለምሳሌ 6፣ 7 መርከቦች ናቸው በአንድ ጊዜ ወደብ ላይ የሚቆሙት፤ 23 ሺሕ ዶላር በ6፣ በ7 ብናባዛ ፤ ይሄን በ7 ወይም በ10 ቀን ብናባዛ ሌላ አንድ መርከብ ማዳበሪያ የምንገዛበትን ገንዘብ ኢትዮጵያ አጣች ማለት ነው ” ብለዋል።
ችግሩ ተደምሮ አርሶ አደሩ ላይ እንደሚወድቅ በመግለጽ ለማዳበሪያ ዋጋ መናር፣ አንዱ ጉዳይ የዓለም ዋጋ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ከዚያ በተጨማሪ የሚመጣው፥ የስርጭት ሂደት ላይ ያለው መጓተት ቸልተኝነት መሆኑን ገልጻዋል።
ልዩ የንቅናቄ እቅድ በማዘጋጀት ያለውን ማዳበሪያ ያለው ሁኔታ ሳይባባስ በአግባቡ ለአርሶ አደሩ እንዲዳረስ በአደራ አሳስበዋል።
ይህ ካልተደረገ ግን በየቀኑ የተሽከርካሪ ምልልስ ከ100 እስከ 110 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚታጣና ችግሩ የሚስተካከለው ደግሞ ማዳበሪያ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ምልልሳቸው ከፈጠነ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተሽከርካሪዎች ምልልስ በየዞኑ፣ በየወረዳው የሚቆም ከሆነ ችግሩ እንደማይቀረፍ ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ “ያ ደግሞ ለእያንዳንዱ መርከብ 23 ሺሕ ዶላር እየበላብን ስለሆነ እባካችሁ፣ ሀገር በዚህ ምክያት ተገቢ ላልሆነ ጉዳት እየተዳረገች ነው” ሲሉ አሳስበዋል።
@tikvahethiopia
