ትናንት ምሽት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት፣ የሲአይኤ ዳይሬክተሩ ጆን ራትክሊፍ እንዲሁም የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄነራል ዳን ኬይን በዋይት ሐውስ መግለጫ ሰጥተዋል።
መግለጫው ያተኮረው አርብ ዐዕለት በኢራን ተመትቶ የተከሰከሰው ተዋጊ ጄት ውስጥ የነበሩ ሁለቱ የአሜሪካ አየር ኃይል አባላትን ለማዳን ስለተካሄደው ዘመቻ ማብራራት ነበር።
የትራምፕ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የበረራ አባላቱን ለማዳን የተደረገውን “ጀግንነት” ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ማክሰኞ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደገና ካልተከፈተ አሜሪካ በኢራን የኃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።
“መላው አገሪቱ በአንድ ሌሊት ሊጠፋ ይችላል፤ ያ ምሽት ደግሞ ነገ ማታ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ኢራን ወደ “ድንጋይ ዘመን” ትመለሳለች ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።
“ድልድይ አይኖራቸውም” ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ምንም አይነት የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም” ሲሉም ዝተዋል።
በዜና መግለጫው ላይ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች እነሆ፡
- ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለይ ሁለተኛውን የአየር ኃይል አባል ፍለጋ ለማግኘት በተካሄደው የ48 ሰዓታት የሕይወት አድን ጥረት ሁሉም የሠራዊቱ አባላት ሙሉ ዕምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
- “በጣም አደገኛ ተልዕኮ” መሆኑ እንደተነገራቸው ያስረዱት ትራምፕ ነገር ግን “የሚገባው እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” ብለዋል።
- አንድ የዜና ተቋም አንድ ፓይለት መጥፋቱን ከዘገበ በኋላ ተልእኮው ችግር ገጥሞት እና ከባድ አድርጎት ነበር ያሉት ትራምፕ የኢራን ባለሥልጣናትም ከዘገባው በኋላ የአየር ኃይል አባሉን ለመያዝ የራሳቸውን ዘመቻ መክፈታቸወን ተናግረዋል። ዋናውን የመረጃ ምንጩን ለማግኘት የአሜሪካ ባለስልጣናት ጠንክረው እየሰሩ ነው ብለዋል።
- ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ከኢራን ጋር የሚደረግ ማንኛውም አዲስ ስምምነት በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ በኩል “ነፃ የነዳጅ ዘይት ፍሰት” መፍቀድን ማካተት አለበት ብለዋል ።
- አሜሪካ የኢራን መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዳግመኛ ከዛቱ በኋላ የአሜሪካ ዘመቻ “ነፃነታቸውን ለማግኘት ለመሰቃየት ፈቃደኞች ለሆኑ” ኢራናውያን ጠቃሚ ነው ብለዋል።
