የኢትዮጵያን የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ቤተሰባዊ ታሪክ የሚዘክረው “Grandpa Was an Emperor” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም በዓድዋ ድል መታሰቢያ መታየት ጀመረ፡፡
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሳበው ፊልም፤ የሚያተኩረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ በሆኑት በልዕልት የሺ ካሳ የግል የሕይወት ታሪክ ላይ ነው።
ፊልሙ በቤተመንግስት ውስጥ የነበረውን የልጅነት የቅንጦት ሕይወት፣ በድንገት የተቀየረበትን የ1966ቱን አብዮት፣ እንዲሁም የቅርብ ቤተሰቦቿ ለዓመታት በእስርና በስደት ያሳለፉትን መራራ ታሪክ በዝርዝር ይተርካል።
ዘጋቢ ፊልሙን ከሌሎቹ የታሪክ ስራዎች ለየት የሚያደርገው፤ ከዚህ ቀደም ለሕዝብ እይታ ያልበቁና በንጉሣዊው ቤተሰብ የግል ካሜራዎች የተቀረጹ ያልታዩ የቪዲዮ ምስሎችንና ፎቶግራፎችን አካቶ መያዙ ነው ተብሏል።
የታዋቂዋ ሲኒማቶግራፈር ኮንስታንስ ማርክስ ስራ የሆነው ይህ ፊልም፤ በታዋቂዋ ድምፃዊትና ተዋናይት ሲንቲያ ኤሪቮ (Cynthia Erivo) አዘጋጅነት (Executive Producer) ለዕይታ የበቃ ነው።
ፊልሙ በፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ የ”Joel Siegel Documentary Award” ሽልማትን ማሸነፉ ይታወሳል።በአሁኑ ወቅት በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኙት ሲኒማዎች ለእይታ ቀርቧል።
