ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎቹና የፖሊሲ አማራጮች
በክቡር ገና
በቅርቡ የጸደቀውን የ582 ቢሊየን ብር ተጨማሪ የፌደራል መንግሥት በጀትን ለጊዜው አቆይተን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ያጸደቀውን የ971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ለርእሰ ጉዳያችን መነሻ አድርገን ጥቂት እንበል፡፡
በወቅቱ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ አመታዊ በጀት አጸደቀች ሲሉ የዘገቡለት ይህ የፌዴራል መንግሥት በጀት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በውጭ ምነዛሪ ተመን ቅነሳ ምክንያት ዋጋው በግማሽ እንዲቀንስ ሆኗል፡፡
እንደ ተለመደው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች “እንኳን ደስ አለን! ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ተሸጋገረች” በማለት አጋነው እንዳቀረቡት ሳይሆን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ተግባራዊ መደረግ በጀመረው በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ምክንያት የሀገሪቱ በጀት በዶላር ሲሰላ ከ17.34 ቢሊዮን ዶላር በአንድ ጀንበር ወደ 8.45 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል፡፡
ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም 3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ሲባል ተግባራዊ የተደረገው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ከሐምሌ 21/2016 ዓ.ም በፊት 56 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር በ115 ብር እንዲመነዘር በመደረጉ የብር ዋጋን ግማሽ በግማሽ በሚያሰኝ መልኩ ለውድቀት ዳርጎታል፡፡
ይህን ብርን የሚያዳክመውን በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚስቶችና የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት ለነጻ ገበያ ሥርዓት መጎልበት መንገድ ጠራጊ ነው ብለው ቢያወድሱትም ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ ሀገሪቱን ወደ ባሰና ወስብስብ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳ መዘዞች
ከውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳ መዘዞች ዋንኛውና ወዲውኑ የሚከሰተው የዋጋ ንረት ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ ያለርህራሄ ቀንበሩን የሚያሳርፈው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችና የወር ደሞዝተኛ በኾኑ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሰራተኞች ላይ ነው፡፡ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል ቢባልም በተለይም በገቢ ምርት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ባላቸውና እንደ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚልኩት ምርት ወደ ሀገር የሚያስገቡት ምርት የትየለሌ በሆነባቸው ሀገሮች የመሠረታዊ ምርቶችን ዋጋ በማናር ፍጹም የማይቀመሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ሆኖ የጸደቀው 971.2 ቢሊዮን በር በውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳ ምክንያት በዶላር ሲሰላ ከ17.34 ቢሊዮን ዶላር ወደ 8.45 ዶላር ማሽቆልቆሉ በዓለም አቀፍ ገበያ የኢትዮጵያን የመግዛት አቅም በግማሽ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ ምርቶችን ማለትም ነዳጅ፣ መድሀኒት፣ ማዳበሪያና የምግብ ዘይት የመሳሰሉትን ወሳኝ ምርቶች ከውጭ በሚያስገባበት ወቅት እጥፍ ዋጋ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ ለምሳሌ ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ከዚህ ቀደም 20 ቢሊዮን ብር ያወጣ የነበረ ከሆነ አሁን 40 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡
ብር ከአቅሙ በላይ ዋጋው ተጋኗል ስለዚህም ዋጋው መስተካከል አለበት በሚል የአንድ ወገን ትንታኔ የብርን የመግዛት አቅም እንዲዳከም ማድረግ በተለይም አንደ ኢትዮጵያ ባለችና የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ዝቀተኛ የሆነ በርካታ ደሀ ዜጎች ባላት ሀገር በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ማኅበራዊ ቀውሶችን ያስከትላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳው ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ ስለሚያንር በተለይ የምግብ ፍጆታ ምርቶችን ዋጋ ይበልጥ ያንራል፡፡ በዚያ ላይ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብ እርዳታ ጥገኛ በሆኑባት ሀገር ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ይከተዋል፡፡
እንደ ዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የወጪ ንግድ በማነቃቃትና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢኮኖሚውን ያሳድጋል የሚል የቆየ አባባል አላቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ግን የውጭ ምንዛሬ ተመን ቅነሳ በማኅበረሰቡ ላይ የሚያስከትለውን የኑሮ ቀወስ አሳንሶ የሚያይ ሲሆን አብዛኛው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ በሚኖርባትና አብዛኛውን መሠረታዊ ምርት ከውጭ ለምታስገባ ሀገር ቀመሩ የሚሠራ አይደለም፡፡
የመንግሥት ዕዳ – የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ወጥመድ
የውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳው ጉዳይ ከሀገሪቱ የውጭ ብድር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑ ነገሩ ሁሉ አዙሪት መሆኑን ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ውጭ ብድር እየጨመረ በመምጣቱ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ለውጭ እዳ ክፍያ 139.3 ቢሊዮን ብር (1.21 ቢሊዮን ዶላር) ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በብድር የተገኘው 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሀገሪቱን የእዳ ጫና ለማስተንፈስ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ለማሳደግና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በሚል የተሰጠ ነው፡፡ ሆኖም ግን ብድሩ ኢትዮጵያን ለውጭ ብድር ጥገኝነት የሚዳርግ ሲሆን ሀገሪቱንም የእዳ ወጥመድ ውስጥ በመክተት ከብድር አዙሪት እንዳትወጣ ቀፍድዶ የሚይዛት ነው፡፡
በውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳው ምክንያት የብር ዋጋ በመዳከሙ ኢትዮጵያ ለውጭ ብድር የምትከፍለው እዳ በብር ሲተመን እጥፍ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ መንግሥት ለውጭ እዳ ክፍያ የሚያወጣው ወጪ በእጅጉ ስለሚጨምር ለማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚመድበውን በጀት እንዲያጥፍ ወይም በጣም እንዲቀንስ ያስገድደዋል፡፡ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚገኘው ብድር የአጭር ጊዜ እፎይታን ቢያስገኝም ብድሩን ተከትሎ የሚመጣው እንደ መዋቅራዊ ለውጥ ያሉ ግዴታዎች ለማኅበራዊ ከለላዎች የሚሰጡ ድጋፎችን እንዲቀንስ በማድረግ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጡ ኒዮሊብራሎች ኢትዮጵያን በመንግሥት ከሚመራ የኢኮኖሚ ሞዴል በገበያ ወደሚመራ የኢኮኖሚ ሞዴል ለማዛወር አቅደውና አልመው ያደረጉት መሻሻያ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ለውጥና እድገት ለማምጣት እንደ የግብርና ምርታማነት፣ የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማትንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የመሳሰሉት ላይ መዋቅራዊ ለውጥን ማምጣት የግድ ይላል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳ ላይ ብቻ የተደረገው ለውጥ ግን ኢትዮጵያን የውጭ ካፒታል ጥገኝነቷን ከማባባሱም በላይ ሀገሪቱን ለከፋ ቀውስ ተጋላጭ ያደርጋታል፡፡
ግጭትና ልማት
ሀገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት በግጭት አዙሪት ውስጥ ስትዳክር ኖራለች፡፡ አንዳንዶቹ ግጭቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉና በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት ያደረሱ ጦርነቶች ናቸው፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች አሉ፡፡ ግጭቶች ካሉ ደግሞ ወታደራዊ ወጪዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በ2017 በጀት ዓመት ለመከላከያ 65.7 ቢሊዮን ብር (571 ሚሊዮን ዶላር) ተመድቧል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ለትምህርት 79.8 ቢሊዮን ብር (694 ሚሊዮን ዶላር) እንዲሁም ለጤና 33.9 ቢሊዮን ብር (295 ሚሊዮን ዶላር) ተመድቧል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላለች ድሀ አገር አብዛኞቹ ዜጎቿ መሠረታዊ የትምህርትና የጤና አገልግሎት በቅጡ ላልደረሳቸው ለወታደራዊም፣ ለትምህርትም፣ ለጤናም ከፍተኛ በጀት እየመደበች ልማትና እድገቷን ማረጋገጥ እንደማትችል ግልጽ ነው፡፡ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ሰላምን ለማስፈንና ደህነትን ለማረጋገጥ ወታደራዊ ወጪዎች የግድ አስፈላጊ ነው ቢሉም በጦርንቱ ወጪዎች ምክንያት የሚታጠፉ የማኅበራዊ አገልግሎቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታንና አመጽን በመቀስቀስ መልሰው ያለመረጋገትና የግጭት መንስኤ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም መንግሥት በግጭትም ውስጥ እንኳ ሆኖ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጡ በሚችሉ በትምህርት፣ በጤናና በሥራ ፈጠራ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
መሠረተ ልማትና ባለሁለት ስለት ሰይፍ ገጽታው
መንግሥት በዚህ ዓመትም ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች 283.2 ቢሊዮን ብር (2.46 ቢሊዮን ዶላር) መመደቡ ከዚህ ቀደም ለካፒታል ፕሮጀክቶች የነበረውን ትኩረት የቀጠለበት መሆኑን ያመላክታል፡፡ የውሀ ልማትና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለብዙ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት አካል ሆነው የቀጠሉ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2004 እስከ 2018 ባሉት ዓመታትም መካከል በየዓመቱ የ10 በመቶ እድገት ማስመዝገባቸው ይታወሳል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ለካፒታል ፕሮጀክቶች 283.2 ቢሊዮን ብር ቢመደብም በውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳው ምክንያት በሚፈጠረው የዋጋ ንረት እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አያስገኙም፡፡ የካፒታል ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉት መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው ለእቃዎቹ ማስገቢያ ቀድሞ ከተያዘው በጀት በላይ የሚጠይቁ በመሆኑ የገንዘብ እጥረት መፈጠሩና በዚህም ምክንያት የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም መዘግየቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ተገባራዊ የሚደረጉ በብድር የሚከናወኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዳይበቁ ከማድረጉም ባሻገር ኢትዮጵያን የእዳ ማጥ ውስጥ ይከታታል፡፡
የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻውን የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግር አይፈታም፡፡ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትዎችን የማልማት፣ የግብርና ምርቶችን የማሻሻልና በየዓመቱ ወደ ገበያው የሚቀላቀሉ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሚሆን ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ ካለተፈጠረና ተግባራዊ ካልተደረገ የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻውን ማኅበረሰቡን ያላማከለና ለማኅበረሰቡ የማይፈይድ ግንባታ ይሆናል፡፡
ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማና ፍትሀዊነት
በ2017 በጀት ዓመት የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ 236.7 ቢሊዮን ብር (2.06 ቢሊዮን ዶላር) መድቧል፡፡ ይህ በጀት በድህነት አረንቋ ለተዘፈቁ የሀገሪቱ ዜጎችና በግጭት ለተጎዱ ክልሎች እንደ የሕይወት እስትንፋስ የሚቆጠር ነው፡፡ ሆኖም ግን በውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳው ምክንያት የብር ዋጋው በተዳከመበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በተፈናቀሉበትና መሠረተ ልማቶች በጦርነት በወደሙበት እንደ አፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ይህ በጀት ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በክልሎች ዘንድ ዘላቂ መረጋጋት እንዲሰፍን በክልሎች መካከል ፍትሐዊ ልማትና እድገት ማረጋጋጥ በጣም አስፈላጊና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በብሔራዊ ደረጃ ለሚመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት አኀዞች ብቻ ሳይሆን በክልሎች መካከል ስላው የሀብት ክፍፍልና ክልላዊ እድገት ትኩረት መስጠትና ከሀገራዊው ሀብት የድርሻቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለማድረግና ለክልሎች ልማትና እድገት ትኩረት አለመሥጠት አለመረጋጋት ከመፍጠሩም በላይ ለግጭት ይዳጋል፡፡
ማጠቃለያ ፡- የአማራጭ ፖሊሲ ጥሪ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የመጣው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና የልማት ጉዞ ላይ ወሳኝ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ተመን ቅነሳ የወጪ ንግድን ያነቃቃል ቢባልም የዋጋ ንረት በፍጥነት እንዲያሻቅብ፣ የተጣራ ገቢ እንዲቀንስና የእዳ ጫና እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ መንግሥት ለመከላከያና ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ከፍተኛ በጀት መመደቡ ከተጨባጩ ሁኔታ አንጻር የምንረዳው ቢሆንም ማኅበራዊ ቀውስን በማባባስ ረገድ የራሱ ሚና እንዳለውም መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋት አካታች እድገት፣ እኩልነትና ማኅበራዊ ፍትሕን በሚዛናዊነት የሚያስተናግድ ስልት ወይም አሠራር ነው፡፡ ሀገሪቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና በኒዮሊብራል ማሻሻያዎች ከመተማመኗ ይልቅ በሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ፣ በኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዲሁም እንደ ትምህርት፣ ጤናና የምግብ ዋስትና በመሳሰሉት ሕዝብ ተኮር ልማቶች ላይ ብታተኩር የተሻለ ይሆናል፡፡ ፈተናዎችን በቀላሉ ማስወገድና ማስተካከል ቀላል ባይሆንም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሞዴል የዓለም አቀፉን የፋይናስ ገበያ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል አድርጎ መቀየስ የግድ ይላል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 220 ታህሳስ 12 2017 ዓ.ም
