በየዓመቱ ትንሣኤ በዋለ 25ኛ ቀን የሚካሔደው ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ መሪነት የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎቱ ይከናወናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሔዳል።
በየዓመቱ የሚካሔዱት ሁለቱ ጉባኤያት አንደኛ ቋሚ በሆነ ቀን በጥቅምት 12 ሲጀምር ሁለተኛው ግን የአጽዋማቱን አዋጅ ተከትሎ በሚወጣው የባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት በዓለ ትንሣኤ በዋለ 25ኛ ቀን የርክበ ካህናት ጉባኤ ይከናወናል።
በዚህ በ2017 ዓ/ም ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነገ ግንቦት 6/2017 ዓ/ም የሚጀምር ሲሆን በዋዜማው ዛሬ ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ሥርዓተ ጸሎቱ ይከናወናል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የፕትርክና መንበሩ ከግብፁ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት ከሰኔ 21/1951 ዓ/ም ወዲህ አስቸኳይ ጉባኤያትን ሳይጨምር ከ131 መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤያት መካሔዳቸውን ታሪክ ያስረዳል።
ከነዚህ መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቅዱሳን ፓትርያርኮች ጥረት ርእሰ መንበርነት የተመሩ ሲሆን በሁለት የተለያዩ ዓመታት ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፓትርያርክ ባለመኖሩ ምክንያት በአቃብያነ መንበር በብፁዓን አባቶች ተመርተዋል።
ከእነዚህ አንደኛው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ በወቅቱ በነበረው አገዛዝ ምክንያት በግፍ ለግዞት ስለተዳረጉ ግንቦት 11 ቀን 1968 ዓ/ም የዋለውን ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቃቤ መንበር በነበሩት በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የመላ ትግራይ ሊቀ ጳጳስ ርእሰ መንበርነት ተመርቷል።
ሁለተኛው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 5ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ነሐሴ 10/2004 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በማረፋቸው ምክንያት የጥቅምቱ 12/2005 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖደስ ምልዓተ ጉባኤን የወቅቱ አቃቤ መንበር የነበሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በርእሰ መንበርነት መርተዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጥበት ሲሆን እምነት የማጽናት ሥርዓትን ማስጠበቅ አስፈላጊ ከሆነም መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች የማሻሻል ሥልጣን ያለው የቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል ነው።
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”
ሐዋርያት ፳፥፳፰
🔵የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
