በአለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዉስጥ ስመጥር የሆነዉ እና በቻይና መንግስት ባለቤትነት የሚተዳደረው የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (ሲሲኢሲሲ) ኢትዮጵያ በቢሾፍቱ አቅራቢያ ለመገንባት ያቀደችውን ግዙፉን አየር ማረፊያ ላይ አሻራውን እንዲያኖር ተጠይቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰዉ፣ ኩባንያው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን በማስታወስ ፤ በአዲሱ አየር ማረፊያ ግንባታ ላይ አብሮ እንዲሠራ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ግብዣ ያቀረበዉ በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤቱ መዋቅራዊ ግንባታ መጠናቀቁ በተገለፀበት በወቅት ነው ። ግንባታውን በማከናወን ላይ ያለው የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው።
አዲሱ የአየር መንገዱ ዋና መሥሪያ ቤት 45 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በ33 ሺ560 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያርፋል ተብሏል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የንግድ፣ የኮርፖሬት እና የደንበኞች አገልግሎትን ጨምሮ ስድስት የተለያዩ ሕንጻዎችን ያካተተ መሆኑን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ግንባታው የተጀመረው እኤአ በነሐሴ 2023 ሲሆን፣ በነሐሴ 2026 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
እኤአ በ1979 የተቋቋመው ሲሲኢሲሲ፣ በተለይም በአፍሪካ ጎልቶ የሚታይ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ሲሆን በኢትዮጵያም በዘርፉ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እንዳለው ይታወቃል።
