በህንድ የኢንዲራ ጋንዲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (IGIA) የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ላይ ባለው ከባድ የሥራ ጫና ምክንያት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የቪስታራ አየር መንገድ አውሮፕላኖች በኅዳር 10 ቀን 2023 አደጋ ሊደርስባቸው ተቃርቦ እንደነበር የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ባወጣው የመጨረሻ ዘገባ ላይ አስታወቀ።
አንድ የ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 አውሮፕላን ሊነሳ ሲዘጋጅ፣ ከጎኑ የ ቪስታራ አየር መንገድ አውሮፕላን ለማረፍ እየተቃረበ ነበር።
በከፍተኛ ነፋስ ምክንያት የቪስታራ አውሮፕላን የማረፍ ሙከራውን ሲያቋርጥ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር ሊጋጭ ተቃርቦ እንደነበር ተገልጿል።
የሁለቱም አውሮፕላኖች የትራፊክ ግጭት መከላከያ ስርዓት (TCAS) “እርስ በእርስ ይራቁ” የሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠት ግጭቱን ማስቀረት ችሏል። እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በሁለቱም አውሮፕላኖች ውስጥ በድምሩ 227 ሰዎች ነበሩ።
የአደጋው ዋና መንስኤ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ከፍተኛ የሥራ ጫና በመኖሩ “አእምሯዊ የመጫን አቅም በላይ” መድረሱ እንደሆነ የምርመራ ሪፖርቱ ገልጿል። ይህም ቅድሚያ መስጠት የሚገባቸውን የደህንነት ተግባራት በአግባቡ እንዳይከታተል አድርጎታል።
ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ አውሮፕላንን የመነሻ ፈቃድ በጊዜው ቢሰርዝ ኖሮ፣ አደጋው ሙሉ በሙሉ ሊወገድ ይችል እንደነበር ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የህንድ የአውሮፕላን ማረፊያ ባለስልጣን ደህንነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን እንዲተገብር ተጠይቋል።
CapitalNews
