የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ስለ ብልጽግና ፓርቲ ምን አሉ?

Date:

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል የብልጽግና ምክር ቤት አርብ ዕለት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ሰኞ ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ብልጽግና “በየጊዜው አሉታዊ እና ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ነው” ሲሉ ወነጀሉ።

አቶ የማነ አክለውም በዚህ “አሳፋሪ ዘመቻ” የኤርትራ ታሪክ፣ ፖሊሲዎች፣ የልማት ዕቅዶች፣ እምቅ አቅም እና ቀጣናው ላይ ያላት ሚና “ከባድ እና ኢፍትሐዊ ጥቃት” እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ጽፈዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 2/2017 ዓ.ም. ሲያካሄድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ “የተራዘመ ጦርነት የተጨናገፈባቸው ጠላቶች” ሲል የገለጻቸው ኃይሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን ለመቀስቀስ እየሞከሩ ነው ብሏል።

ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው ላይ “ጠላቶች” ሲል የገለፃቸውን በስም ባይጠቅስም፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኞችን” በመጠቀም የሕዝብን እና የመንግሥትን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የተዋጋው የኤርትራ መንግሥት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ወዳጅነቱ ተቀዛቅዞ በአሁኑ ወቅት ለጦርነት በመዘጋጀት በመካሰስ ላይ ናቸው።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የብልጽግና ምክር ቤትን መግለጫ በቀጥታ ባይጠቅሱም ኤርትራ ኢትዮጵያ ላይ የቆየ ጥላቻ ስላላት “የኢኮኖሚ ግስጋሴዋን ለማደናቀፍ” ስለመባሉ ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ አገራቸው የሁሉንም አገራት ዕድገት እና ብልጽግና በጽኑ እንደምትደግፍ ገልፀው በቀጠናው ላይ የምተከተለው ፖሊሲ እና ዕድገት “ሁሉም የሚከስርበትን” መንገድ አይደለም ብለዋል።

ኤርትራ በታሪኳ ሀብቷን እና መሬቷን በኃይል ለመውሰድ ከሚፈልጉ አካላት የተለያዩ ዛቻዎችን ማስተናገዷን እና ጦርነቶች ማድረጓን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ “የኤርትራ የረዥም ጊዜ አቋም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንደተናገሩት ‘የሌሎችን አንፈልግም፣ የራሳችን የሆነውንም አሳልፈን አንሰጥም’ ” ብለዋል።

በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው በማለት ከተናገሩ እና ይህንንም በተመለከተ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ተከትሎ ኤርትራ ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለንጣዎች ጋር የጋራ ትብብር ፈጥራለች።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ በቅርቡ ለአገራቸው ብሔራዊ የቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ኢትዮጵያ ዕለት ተዕለት በጦር ኃይል እያስፈራራች እንዲሁም የጦር መሳሪያ እየገዛች ነው በማለት መክሰሳቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በኤርትራ በኩል ውጊያ እንደሚነሳ በርካታ ወሬዎች እንደሚነገሩ ጠቅሰው “በእኛ በኩል አንዲት ጥይት አይተኮስም” ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀዋል።

አክለውም “የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው። የእኛን ሰላም መፈለግ በዚያ ምጥጥን መታየት አለበት” ሲሉ አስረድተዋል።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር በትዊተር ልጥፋቸው አገራቸው በተፈጥሮ ሃብቶች እና ታታሪ ሕዝቦችን መታደሏን አንስተው ይህ “ሰላም በሰፈነበት ክልላዊ ሁኔታ ውስጥ ፈጣን እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያረጋግጥ ይቸላል” ብለዋል።

አክለውም “እነዚህን እውነታዎች ድብቅ አጀንዳዎችን ወደፊት ለመግፋት ሐሰትን እና የፈጠራ ትርክቶችን በመደጋገም ሊጠፉ አይችሉም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሁለት አስርታት በላይ በፍጥጫ ውስጥ ከቆዩ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸው ቢሻሻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በመካከላቸው ያለው ቅራኔ እየጎላ መጥቷል።

ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ላይ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመቆም የተሳተፈች ሲሆን፣ ደም አፋሳሹ ጦርነት በፕሪቶርያ ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ መጥቷል።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል።

ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ትብብር መፍጠሯን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል።

በተጨማሪም በይፋ ባይነገርም ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ የምትከሰስ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የኤርትራ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት መክፈት እና ስብሰባ እስከማካሄድ ደርሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተቃቃረው እና ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ስለመፍጠራቸው በስፋት እየተነገረ ይገኛል።

ከ25 ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ምክንያት ጦርነት ውስጥ ገብተው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞቱበት ጦርነት በኋላ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሌላ ዙር ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አይሏል።

BBC Amharic

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...