የጤና ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በመላ አገሪቱ የእናቶች፣ የጨቅላ ሕፃናት እና የሕፃናት (RMNCH) ጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከር የሚያስችል ታሪካዊ የፋይናንስ ስምምነት ተፈራርሟል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ የጤና ፋይናንስን ለመገንባትና የዜጎችን የጤና ውጤት ለማሻሻል ትልቅ እርምጃ ነው።
በዚህ ስምምነት የልማት አጋሮች 171.2 ሚሊዮን ዶላር ቃል የገቡ ሲሆን፣ መንግስትም አገራዊ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ቀሪውን ኢንቨስት በማድረግ ጠቅላላ በጀቱን ወደ 282.4 ሚሊዮን ዶላር አሳድጎታል። ይህም ለዘርፉ ከሚያስፈልገው ሀብት 92 በመቶውን የሚሸፍን ነው።
ይህ ስምምነት የዓለም ባንክ፣ ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እና ዩኒሴፍን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሳተፉበት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
ስምምነቱ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
