የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች እና የ2018 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ የአሰራር ችግሮች ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየሆኑ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ጥቂት ተቋማት ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግና ለሀገራዊ ችግሮች ምሁራዊ መፍትሄ ከመስጠት ረገድ ተቋማቱ አሁንም ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ካሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች አንጻር፣ ዩኒቨርስቲዎች ለሀገር እድገትና መረጋጋት ያላቸውን ሚና ለመወጣት በአዲስ ሞራልና ትጋት ሊጠናከሩ እንደሚገባም ተመላክቷል።
በሌላ በኩል፣ የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ እንደገለጹት፤ የትምህርት ሚኒስቴር የተቋማቱን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተል የዘረጋው አሰራር ችግሮችን ለመረዳትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል። ይህ መድረክ ዩኒቨርስቲዎች በቴክኖሎጂና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ልምድ እንዲያጋሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የጀመረውን የተቀናጀ የክትትል ስርዓት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ታውቋል።
