ቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በማህበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ስራዎች ለመስራት አርቲስት አለማየሁ ታደሰ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆነ።
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ የቲቢ በሽታን የግንዛቤ ስራ ለመስራት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆኖ በጤና ሚኒስቴር ተሰይሟል።
ሀገራችን የቲቢ በሽታ ጫና ካለባቸው የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን የጠቀሱት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ ቲቢ ልንከላከለው የምንችለው በሽታ በመሆኑ አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ባለው የህብረተሰብ ተቀባይነት ተጠቅሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት የበሽታውን ጫና እንደሚቀንስ ተስፋ አለኝ ብለዋል።
ለመረጃ ቅርብ በሆኑት የሚዲያ ባለሙያዎች እንኳን ስለ ቲቢ ያለው ግንዛቤ በቂ አለመሆኑን የጠቆመው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ በበኩሉ፤ የወጣሁበትን ማህበረሰብ ማገልገል ግዴታየ ነው፤ ቲቢን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ለመስራት በመመረጤ ደስ ብሎኛል፤ የምችለውን ያህል በመስራት ግዴታዬን እወጣለሁ ብሏል።
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ ለረዥም አመታት ብሄራዊ የቲቢ በሽታ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆኖ ማገልገሉ ይታወሳል።
