የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን “ዘመናዊ” የጦር መሳሪያዎችን በኔቶ አባል ሀገራት በኩል እንደምትልክ አስታወቁ።
ትራምፕ ይሄን ያሉት ከኔቶ ዋና ፀሃፊ ማርክ ሩት ጋር ትናንት በዋሽንግተን ኦቫል ኦፊስ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ነው።
በውይይታቸውም ሚሳኤልን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው ትራምፕ ያስታወቁት ።
ትራምፕ፣ “ዩክሬን የምትፈልገውን ማድረግ እንድትችል ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ሲሉ ከሩት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ተናግረዋል።
የኔቶ ዋና ፀሃፊ ማርክ ሩት በበኩላቸው፣ አሜሪካ “በኔቶ በኩል ለዩክሬን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በከፍተኛ መጠን ለማቅረብ” መወሰኗን አረጋግጠዋል። የአውሮፓ ሀገራትም የዚህን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ወጪ እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።
ትራምፕ እንዳሉት፣ የአውሮፓ ሀገራት ዩክሬን የሩሲያን የአየር ጥቃቶች ለመመከት የምትጠቀምባቸውን የፓትሪዮት የአየር መከላከያ ስርዓቶች ለኪየቭ የሚልኩ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ ለእነዚህ ስርዓቶች ምትክ እንደምትልክ አስታውቀዋል። ይህ አዲስ ስምምነት የዩክሬንን የመከላከያ አቅም ለማሳደግ እና በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
ትራምፕ በተጨማሪም ሩሲያ በ50 ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ላይ ካልደረሰች ከባድ ቀረጥ እንደሚጣልባት አስጠንቅቀዋል።
ይህ ታሪፍ “ሁለተኛ ደረጃ ታሪፍ” (secondary tariffs) እንደሚሆን የገለጹት ፕሬዝደንቱ፣ ይህም ዒላማው በቀጥታ ሩሲያ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከሩሲያ ጋር በሚነግዱ ሀገራት ላይ በማተኮር ሞስኮን ከአለም አቀፉ ኢኮኖሚ ለማግለል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በሩሲያ ምርቶች የሚጣለው ታሪፍ 100 በመቶ ሊሆን እንደሚችል ትራምፕ አስጠንቅቀዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
