የጋና መንግሥት አዳዲስ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎችን ከውጭ ውድድር ለመጠበቅና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በየብስ ድንበሮች የሚደረግ የፓስታ ገቢ ምርትን አገደ።
ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ በቅርቡ በ40 ሚሊዮን ዶላር የተገነባውን የኦላም አግሪ የፓስታ ፋብሪካን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፣ ውሳኔው የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ለማጠናከር ያለመ ነው።
ፋብሪካው በዓመት 40 ሺህ ቶን ፓስታ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን 40 በመቶ ፍላጎት ይሸፍናል ተብሏል።
ከፓስታ በተጨማሪም እንደ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ስኳር እና ጨርቃጨርቅ ያሉ ምርቶች በየብስ እንዳይገቡ ተከልክለው በባህር ወደቦች ብቻ እንዲገቡ ተወስኗል።
የግብርና ምክትል ሚኒስትር ጆን ዱሜሎ በበኩላቸው፣ ከጎረቤት ሀገራት የሚገቡ ህገ-ወጥ ምርቶች የሀገሪቱን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየጎዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዲሱ አሰራር የመንግሥትን የገቢ ፍሰት ለማሳደግና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አረጋግጠዋል።
