በአፍሪካ ከ52 ሚሊየን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለማምጣትና በሁሉም ዘርፎች እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ‹‹ማካተትን ማድመጥ›› በሚል መሪ ቃል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከመንግስት እና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ፤ቴክኖሎጂ የአካል ጉዳተኞችን ድምፅ ለማሰማትና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ያለውን ሚና አጽንኦት ተሰጥቶታል።
በውይይት መድረኩ እንደተነሳው ለረጅም ጊዜ አካል ጉዳተኞች ከፖሊሲ ቀረጻ ጀምሮ እስከ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ድረስ በበቂ ሁኔታ ሳይካተቱ መቆየታቸው ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ይህንን አካሄድ በመቀየር፤ አካል ጉዳተኝነትን ከውክልና ባለፈ ወደ እውነተኛ ተሳትፎ ለማሸጋገር ጥረት እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና የቮዳኮም አፍሪካ ተወካዮች እንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኝነትን ማካተት እንደ በጎ አድራጎት ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊታይ ይገባል።
‹‹ስለ እኛ ያለ እኛ ተሳትፎ ምንም ነገር አይወሰን›› የሚለውን መሪ ቃል በመጥቀስ፤ማንኛውም የቴክኖሎጂ ውጤትም ሆነ አገልግሎት ገና ከጅምሩ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው፤ መንግስት አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በጤናና በስራ ዕድል እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እንደ ሳፋሪኮም ያሉ የግል ኩባንያዎች ይህንን አጀንዳ በቁርጠኝነት መያዛቸውን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ ‹‹ዲጂታል መገለል አዲስ እየመጣ ያለ ፈተና ነው። ቴክኖሎጂ ለሁሉም በሚመች መልኩ ካልተቀረጸ፣
አካል ጉዳተኞችን ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያገላል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በስራ ቅጥርም ሆነ በአገልግሎት ተደራሽነት ለማካተት የሚያደርገው ጥረት ለሌሎች ኩባንያዎች አርአያ የሚሆን ነው›› ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያመለክተው፣ በአፍሪካ ከ52 ሚሊየን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ። እነዚህ ዜጎች ተገቢውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ካገኙ የሀገርን ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የሚችሉ የሰው ኃይሎች መሆናቸው ተገልጿል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በበኩሉ፤በቮዳኮም ግሩፕ ያለውን ልምድ በመጠቀም አገልግሎቶቹን አካል ጉዳተኞችን በሚያካትት መልኩ እያሻሻለ እንደሚቀጥልና ለዚህም ከኢትዮጵያ መንግስትና ከማህበራት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጧል።
በመጨረሻም ‹‹ማካተትን ማድመጥ›› ማለት ማንም ሰው ከዲጂታሉ የወደፊት ጉዞ ወደ ኋላ እንዳይቀር ማድረግ መሆኑን በመድረኩ ላይ መልዕክት ተላልፏል።
