በኢትዮጵያ ባሉ ሆስፒታሎች እየተስተዋለ የሚገኘውን የኦክስጅን እጥረት ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኦክስጅን እጥረት በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ያነሳው ሚኒስቴሩ፤ ከዚህ በፊት ፈቃድ ወስደው ኦክስጅን በማምረት ላይ ከሚገኙት 40 ተቋማት በተጨማሪ የማምረቻ ማሽኖችን በየአካባቢው በመትከል ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ወደየአካባቢው ለማድረስ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የሕክምና አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ የሆስፒታል ዲያጎንስቲክ ዴስክ አስተባባሪ ዐቢይ ዳዊት፤ በኦክስጅን ስርጭት ላይ የሚታየው ችግር የምርት እጥረት ብቻ ሳይሆን ምርቱን ወደየ ሆስፒታሎቹ እና አገልግሎት ፈላጊዎች የማድረሻ ሲሊንደር እጥረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኦክስጅን ከማምረቱ ጎን ለጎን አዳዲስ ሲሊንደሮችን ለማምረትም ሂደቶች መጀመራቸውን ያነሱት ኃላፊው፤ “በተለይ ጥሩ የኤሌትሪክ አቅርቦት ባለባቸው አካባቢዎች በመጠኑ አነስተኛ የሆነና በቀላሉ የሚንቀሳቀስ ‘ኦክሲጂን ኮንሰንትሬተር’ የተባለ መሳሪያ እየተጠቀምን እንገኛለን” ብለዋል።
በዚህም መሠረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኦክሲጅን ማምረቻ ማሽኖችን በየአካባቢው በመትከል ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ወደየአካባቢው ለማድረስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
ኦክስጅን ለሕክምናው ዘርፍ ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፤ ሕጻናት በኒሞኒያ በሽታ ሕይወታቸው እንዳያልፍ፣ ከመተንፈሻ አካል ሕመም ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ችግር፣ በተለይም በቀዶ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በድንገተኛ አደጋ ወቅት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
