በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ጋዜጦችን በዲጂታል መልክ ለማቅረብ ሥራዎች ስለመጀመራቸ የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አስታውቋል።
ይህም የሆነበት ምክንያት በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰው የዲጂታል መንገዶችን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፤ ጠቃሚ የሆኑ ፅሁፎችን በተለያዩ አማራጮች ለሐዝብ ማቅረብ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ በአገልግሎቱ የባህረጥበባት ባለሙያ እንግዳወርቅ ቢያዝን ገልፀዋል።
መፅሐፍትን በዲጂታል መልክ ከማቅረብ ጋር በተያያዘ በቤተመፅሐፍቱ ከሚገኙት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑ መፅሐፍቶች በዲጂታል መልክ ተዘጋጅተው መቅረባቸውን ገልጸው፤ በዛ መልክ ሳይዘጋጅ የቀሩት ጋዜጦች ብቻ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁሉንም አይነት ጋዜጦችን በዲጂታል መልክ ለማዘጋጀት በተጀመሩ ሥራዎች ውስጥ የአዲስ ዘመን ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ እትሞች በቀዳሚነት እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ እንደሚያልቅ የገለጹት ባለሙያዋ፤ “ማንኛውም ሰው በቤተመፅሐፍቱ ግቢ ውስጥ በመግባት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት ብቻ በመጠቀም” ማንኛውንም አይነት መፅሐፍ ማንበብ እንደሚችል ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም ከዲጂታሉ ባሻገር በወረቀት የሚታተሙ መፅሐፍትን የማንበብ ልምድ ለማዳበር ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ጭምር በክልል ከተሞች በመሄድ የንባብ ሳምንቶች እየተዘጋጁ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እየተሰሩ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም ወደ ጋራ መኖሪያ ቤቶች በየ15 ቀኑ በመሄድ የሚያስፈልጋቸውን የመፅሐፍ አይነትና የባለሙያ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
(አሐዱ ሬድዮ)
