የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን መዳረሻቸውን በማዘግየት እና ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የነዳጅ ስርጭት ችግር የፈጠሩ 254 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ላይ የ116 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደጣለ አስታወቀ። በተጨማሪም 354 የነዳጅ ማደያዎች ላይ በክልሎች በኩል ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጿል።
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ደስታው መኳንንት እንደተናገሩት፣ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች የተቀበሉትን ነዳጅ በወጣላቸው የዋጋ ተመን መሸጥ ሲገባቸው፣ ዋጋ ጨምረው በህገወጥ መንገድ ይሸጣሉ። የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎ ጭማሪ ይኖራል በሚል ግምትም ነዳጅ በመደበቅ የችግር መንስኤዎች ናቸው።
ከዲጂታል ሽያጭ ውጪ በእጅ በእጅ ሽያጭ ባከናወኑ 526 ማደያዎች ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን፣ ከድርጊታቸው ያልታቀቡት 354 ማደያዎች ላይ ደግሞ በክልሎች በኩል ክስ ተመስርቶ በሂደት ላይ ይገኛል።
