ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከሲቪል አቪሽን ባለስልጣን እውቅና ባገኘበት በአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያንነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን፤ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር አስመርቋል።
በዚህም ዘርፍ የመጀመሪያውን ባች በማስመረቅ ብቸኛው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሆን መቻሉን አስታውቋል።
በተጨማሪም ኮሌጁ በድህረ-ምረቃ፣ በቅድመ ምረቃ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እና በሰርተፊኬት ፕሮግራሞች ለ12ተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዚሁ መርሃ ግብር ላይ አስመርቋል።
ኮሌጁ ለአስራ ሁለተኛ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በኢንተርናሽናል ትሬድ እና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በሎጅስቲክስ እና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት 130 እጩ ተመራቂዎችን፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም በአቬሽን ማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ፣ በሆቴል ማኔጅመንት እና በማርኬቲንግ ማኔጅመንት 93 እጩ ተመራቂዎችን ነው በዛሬው ዕለት ያስመረቀው።
እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በደረጃ 5 በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በፍሮንት ኦፊስ፣ በሀርድዌርና ኔትወርክ ሰርቪስ፣ በማርኬቲንግና ሴልስ ማኔጅመንት፣ በነርሲንግ እና ፋርማሲ 1 ሺሕ 35 ሰልጣኞችን አስመርቋል።
በሠርተፍኬት ስልጠና መርሃ ግብር ደግሞ፤ በኤርክራፍትና ሜንቴናንስ ቴክኒሻን ፓወር ፕላንት፣ በኤር ፍሬም፣ በአቪኦኒክስ፣ በኤርላይን ካቢን ክሪው፣ በፍላይት ኦፕሬሽን ኦፊሰር እና በቲኬቲንግና ሪዘርቬሽን ያሰለጠናቸውን 370 ሰልጣኞችን በጠቅላላ 1 ሺሕ 628 እጩ ተመራቂዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል
ኮሌጁ የስልጠና ዘርፎችን በማስፋት በጤናው ዘርፍ በቅድመ ምረቃ ደረጃ በነርሲንግና በፋርማሲ ስልጠና መስጠት መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል እና የናሽናል ኤርዌይስ እህት ኩባንያ እንደሆነ በመድረኩ ተነግሯልል።
ናሽናል ኤርዌይስ፣ በኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች መካከል ግንባር ቀደሙ ሲሆን፤ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የመንገደኛና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል።
