ዛሬ ዓለም አቀፍ የተራራ ቀን ነው – ተራራ እወዳለሁ፤ ለተራሮቻችን ህልውና ድምፄን አሰማለሁ

Date:

ታድለናል፤ የተራራ ሀብታም ሀገር አለን። ሀገሬ ለአፍሪካ ኔፓል ናት። ከሶስት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው የኢትዮጵያ ተራሮች ብዙ ናቸው። ደግሞ ተራራ ብቻ አይደሉም። እንደ ጋራምባ ባህል አኑረዋል። እንደ ቁንድዶ የዱር ፈረስ ሸሽገዋል፣ እንደ ስሜን ቅዱስ ሰውረዋል፣ እንደ አቡነ ዮሴፍ ሰውና ጭላዳ ታርቆባቸዋል።

የሀገሬ ተራሮች ታሪክ ናቸው። እንደ አምባላጌ ድል ፅፈው፣ እንደ ቧሂት ዘመን ዘክረው፣ እንደ ወህኒ አምባ ታሪክ ሰንደው ይኖራሉ። የእምነት ዓምባ ናቸው ስል እስላምጌን ምስክር ግሸንን ማስረጃ አቅርቤ ነው።

ደግሞ ውበት ናቸው፤ ደጀንና ቱሉ ዲምቱን ያየ ይሄንን አይሞግትም። ምትሃትም ናቸው ጭላሎና ጮቄ ለቆመ የምለው ይገባዋል። ወግ ተሞልተዋል መገዘዝ እና ዳቲ ወለል ገና ተደምጠው አልተጠገቡም።

ኢትዮጵያ ተራራዋ ከሰው አይነጠልም። እንደምን ጉጌ ከጋሞ ይለያል? እንደምንስ ጉናን ከበጌምድር እንነጥለዋለን? ይልቅስ ማማ ናቸው እንደ ሙሳ ዓሊ ሩቅ የምናይባቸው። እንደ አቡዬ ሜዳ ምድር የምንቆጥርባቸው።

ስለ እኛ ይናገራሉ፤ አሲምባ ኢሮብን ይተርካል፣ ዘቢደር የጉራጌ አንደበት ነው፣ አዘሎ አፋርን ያወጋል፣ ጨርጨር ሸጎዬ ያስደምጣል፣ ሙጎ የስልጤ አንደበት ነው፤ ጋራ ሙለታ ደግሞ የሀረርጌ ዜማ። እናም ተራሮቻችን ድምፅ አላቸው።
ዓለም ስለ ተራሮች ደህንነት ይህንን ቀን ስለ ተራራ እናስብ ዘንድ በየዓመቱ ያከብረዋል። የዘንድሮው መሪ ቃል “Glaciers matter for water, food and livelihoods in mountains and beyond.” የሚል ነው።

እኛ ተራራ አለን እንጂ ተራሮቻችን ሰው አለን እንዲሉ አላደረግንም። ይታረዛሉ፣ ይጎሳቆላሉ። ለውሃ፣ ለምግብና ለኑሮ አስፈላጊ ናቸው። የሚለው ምን ያህል እንደ ህዝብ የተረዳነው እንደሆነ አላውቅም። ግን እጠይቃለሁ? ከተራራው በታች የኖርንው በተራራው ፀጋ ነው።

ተራሮች በውሃ ዑደት ውስጥ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የበረዶ ግግር በረዶዎች በቀዝቃዛው ወቅት ውሃ ያከማቻሉ፣ ከዚያም በጸደይና በበጋ ወቅት አቅልጠው ውሃ ይለቃሉ። የዓለም ዋና ዋና ወንዞች የሚጀምሩት በተራራ ሰንሰለቶች ነው። እነዚህ ወንዞች በታችኛው ክፍል ለሚኖሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኑሮ መሰረት ናቸው።

የአየር ንብረት ለውጥ ይህንን ሚዛን አደጋ ላይ እየጣለ ነው። ግግር በረዶዎች እንደ የውሃ ማማ ሆነው ያገለግላሉ፣ ነገር ግን እየቀለጡ ነው። አንዴ ከጠፉ በኋላ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት ላይ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ ይሆናል።

ያለ ተራሮቻችን የሜዳዎቻችን መልክ ይህንን ባልመሰለ ነበር። ተራሮቻችንን ጥሩ አድርገን ከያዝን ከተራራው በታች ጥሩ ኑሮ እንኖራለን። ተራሮቻችን ቸር ናቸው ትኩረት ነፍገናቸው ህይወት አልነፈጉንም።

ወንዞቻችን የተራሮቻችን ስጦታ ናቸው። ያለ ውሃ ምንም ነን። የሚታረዝ ተራራ ልብስ የማያለብስ ህዝብ ችግር እርቃኑን ያስኬደዋል። እናም ተራሮቻችንን አረንጓዴ ማልበስ አለብን። የተራሮቻችን ጤንነት ከየግላችን ጤና ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህ ነው ስለ ኢትዮጵያ ተራሮች የምጮኽው።

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የተላለፈ ጥሪ

በክልላችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣው የተሳሳተ ስሌት የወለደው...

በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ  የተኩስ ልውውጥ ተካሄደ

ለዓለም የንግድ ሰንሰለት እጅግ ስትራቴጂካዊ በሆነው የሆርሙዝ ባህረ ወሽመጥ...

የሲ.ኤን.ኤን መስራች ቴድ ተርነር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የዓለማችን ግዙፍ የዜና አውታር ሲኤንኤን መስራች ቴድ ተርነር በ87...

የኢትዮጵያ አጠቃላይ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ይፋ ሆኗል

ኢትዮጵያ  በድጋፍ መልክ ከአሜሪካ በየዓመቱ  በመንግስት በኩል ፈሰስ የሚደረግ...