በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ፍሊፐር ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፣ ከሰራተኞች ጋር በገባው የደመወዝ እና የሥራ ሁኔታ አለመግባባት ሳቢያ በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰ መሆኑ ተነገረ።
ይህ አለመግባባት የተከሰተው ደቡብ አፍሪካዊው ADvTECH ግሩፕ ትምህርት ቤቱን በ7.5 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ በገዛበት ከአንድ ዓመት በኃላ ነዉ።
ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በአምስት ቅርንጫፎች የሚያስተምረው ይህ ትምህርት ቤት፣ ላለፉት ወራት በደመወዝ ማስተካከያ እና በሥራ ጫና ምክንያት በውጥረት ውስጥ ይገኛል። መምህራን እንደሚሉት የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም፣ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር በኩል ተገቢው ምላሽ አልተሰጠም።
በዚህም ምክንያት መምህራን በትምህርት ገበታቸው ላይ ቢገኙም፣ በቂ ዝግጅት እና ተነሳሽነት ሳይኖራቸው የሚያስተምሩበት ሁኔታ መፈጠሩን ወላጆች ለካፒታል ጋዜጣ ገልጸዋል።
“ልባቸው የተሰበረ መምህራን ማስተማር አይችሉም” ያሉ አንድ ወላጅ፣ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩን አክለው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በላንቻ አካባቢ የሚገኘው የትምህርት ቤቱ ቅርንጫፍ ተጨማሪ ፈተና ገጥሞታል። የትምህርት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ አስፋው ለካፒታል እንደገለጹት፣ ግቢው ያረፈበት መሬት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ ተላልፎ ለኦሮሚያ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሰጥ ተወስኗል።
ትምህርት ቤቱ እስከ 2025/26 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ድረስ ብቻ እንዲቆይ የተፈቀደለት ሲሆን፣ እስካሁን አማራጭ ቦታ አለመገኘቱ የወላጆችን ስጋት አባብሶታል።
