በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት ታሪካዊው አፍሪካ አዳራሽ፣ ላለፉት አስር ዓመታት የተደረገለትን የ57 ሚሊዮን ዶላር መጠነ-ሰፊ እድሳት ተከትሎ የ2026 የዓለም አቀፍ የሥነ-ሕንጻ ጥበቃ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ተገለፀ።
ይህ በየሁለት ዓመቱ የሚሰጠው ታዋቂ ሽልማት፣ የአውስትራሊያው የሕንጻ ድርጅት አርክቴክተስ የአዳራሹን ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ ለዘመኑ በሚመጥን መልኩ ስላደሰውና ስለጠበቀው የተሰጠ ነው። ይህም ሽልማቱ እ.ኤ.አ በ2008 ከተጀመረ ወዲህ በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ሕንጻ ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ባለፈው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም፣ አፍሪካ አዳራሽ በቺካጎ አቴኒየም – የሥነ-ሕንጻና ዲዛይን ሙዚየም እንዲሁም በአውሮፓ የሥነ-ሕንጻ፣ ጥበብና ዲዛይን ጥናት ማዕከል አማካኝነት በሚሰጠው የ2025 ዓለም አቀፍ የሥነ-ሕንጻ ሽልማት ላይ በ “እድሳትና ጥበቃ” ዘርፍ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።
የሽልማቱ ዳኞች ሰብሳቢና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰር የሆኑት ባሪ በርግዶል እንደገለጹት፣ “አፍሪካ አዳራሽ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የመውጣት ወቅት የአህጉሪቱን ተስፋና ነፃነት ያንጸባረቀ የዘመናዊ ሕንጻ ጥበብ ምሰሶ ነው።”
ሕንጻው በጣሊያናዊው አርክቴክት አርቱሮ መዜዲሚ ተቀርጾ እኤአ በ1961 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት የተመረቀ ሲሆን፣ በውስጡም የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ታዋቂ የቆርቆሮና የመስታወት ስራዎች ይዟል።
በአርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተሰራውን ግዙፍ የቆርቆሮ መስታወት ስራ፣ የአርቲስቱ የልጅ ልጅ በሆነው ባለሙያ አማካኝነት በጥንቃቄ እንዲታደስ መደረጉ ይታወቃል።
ይህ ሽልማት በይፋ የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በፓልም ስፕሪንግስ ካሊፎርኒያ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት ላይ ለዲዛይን ቡድኑ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካ አዳራሽ የየተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) መቀመጫ ከመሆኑ ባለፈ፣ ለጎብኚዎች ክፍት የሆነ ሙዚየም እና የጉብኝት ማዕከል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
