የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የተያዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በግለሰቦች እና በቡድን የሥልጣን ጥም ምክንያት እንቅፋት እየገጠማቸው መሆኑን ገለጹ።
አቶ ጌታቸው በፌስቡክ ገጻቸው በትግረኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተፈናቃዮችን ለመመለስ እና ግዛታዊ አንድነትን ለማረጋገጥ በሚል ስም ሕዝብን ዳግም ወደ ጦርነት የሚከቱ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮችን በዘላቂ ሰላም መመለስ እና ዳግም ግንባታ ማካሄድ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እና የውጭ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ አማራጮችን በማጥበብ ትግራይን ዳግም የጦር ሜዳ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
የአመራሩን ወታደራዊ ስልት የተቹት አቶ ጌታቸው፣ የወጣቱን ሕይወት እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም እና ያለ ከባድ መሣሪያ ሽፋን እግረኛ ሰራዊቱን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ አካሄድ እየተከተለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ወታደራዊ አመራሩ “አለን” ለማለት ብቻ የሚከፍለው ትርጉም የለሽ መስዋእትነት መሆኑን ገልጸዋል።
ተጋዳላዩ ሕዝባዊ ዓላማው ለርካሽ የፖለቲካ ሸቀጥ እንዳይውል ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጠየቁት አቶ ጌታቸው፣ በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘው የፕሪቶሪያ ስምምነት በሰላማዊ መንገድ እንዲተገበር እና ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ተጋዳላዩ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መራሕቱ አሁን የጀመሩትንና ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያመራ የሚችለውን እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ በማሳሰብ “ራሳቸው የለኮሱትን እሳት ራሳቸው ይሙቁት” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
