ከኢትዮጵያ ግዛት የሚነሱ ድሮኖች ጥቃት ፈጽመውብኛል ሲል የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላቀረበው ጠንከር ያለ ክስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት “ፍጹም መሰረት የሌለውና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል ምላሽ ሰጠ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሱዳን አምባሳደር አስጠርቶ በሰጠው ማብራሪያ፤ ውንጀላው ሱዳን “የኢትዮጵያ አማጽያንን ትመልምላለች፣ ትደግፋለች” በሚል የሚቀርብባትን ወቀሳ ለማድበስበስ የተነዛ የሀሰት ወሬ ነው ብሎታል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ባለው ግጭት ገለልተኛ መሆኗንና ሰላም እንዲሰፍን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት በማረጋገጥ፣ የሱዳን መንግስት በተለይ ለ”ሳምሪ” እና ለሌሎች ታጣቂዎች የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ስትወተውት ቆይታለች።
ከወራት በፊት ከፍተኛ የመንግስት ልዑክ ወደ ፖርት ሱዳን በማቅናት ከጀነራል አል ቡርሃን ጋር ተወያይቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከሱዳን ወገን የሚፈለገው አዎንታዊ ምላሽ ባለመገኘቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በጥርጣሬና በውጥረት ውስጥ ይገኛል።
