ቴዲ የወሰደዉን ብር ከነወለዱ 33 ሚሊዮን ብር ለሰዋሰው መልሷል

Date:



በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ ዛሬም ድረስ ስሙ በጉልህ የሚነሳውና በርካታ አድናቂዎች ያሉት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከ9 ዓመታት በኋላ  አዲስ አልበም ነገ ለአድማጮቹ ያቀርባል።

አርቲስቱ ” ኢትዮጵያ ” የተሰኘውን አልበሙን የዛሬ 9 ዓመት ለአድማጩ ካደረሰ በኋላ ነገ ” ኢትዮሪካ ” የተሰኝ አልበሙን በራሱ የዩትዩብ ቻናል ላይ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ማዳመጫ ድረገጾች ላይ እንደሚለቅ ተገልጿል።

አልበሙ ምንም እንኳን ” ሰዋሰው መልቲሚዲያ ” በተሰኘው የዘፈን አቅራቢ ድርጅት በኩል ለህዝብ ይደርሳል ተብሎ ቢነገርም በመካከል አለመግባባት ተፈጥሮ በራሱ መንገድ ወደ አድማጭ እንደሚያደርሰው ነው የተሰማው።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይህን አለመግባባት አጀንዳ ያደረጉና ያራገቡ የተለያዩ ገጾች ጉዳዩን ቀጥታ ከፖለቲካ ጋር እንደሚያያዝ ሲገልጹና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከርመዋል።

ስምምነቱ የፈረሰው ለምድነው ?

እንደ ” ኢትዮፒካሊንክ ” የመዝናኛና መረጃ የሬድዮ ፕሮግራም ከሆነ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት ነው ያፈረሰው።

ስምምነቱ የፈረሰው በአሳታሚውና በአርቲስቱ በኩል ውል ውስጥ የተካተቱት አዳዲስ ጉዳዮች ልዩነት ለመፍጠራቸው ነው።

ሁለቱ አካላት ከአራት አመት በፊት ነው ስምምነት የተፈራረሙት። ውሉን ለማደስ በነበረ ሂደት ግን አዳዲስ ሃሳቦች በመግባታቸው አለመግባባቶች ተፈጥረዋል።

ሰዋሰው በአዲሱ ውል ላይ ቀደም ያሉ የቴዴ አፍሮ ዘፈኖችን በሰዋሰው መተግበሪያ ላይ እንዲጫኑና ለዚህም በየአመቱ የሚከፈል ገንዘብ በቅድመ ክፍያ ለመክፈል ፍላጎቱን ገልጿል።

ይህ ሃሳብ ግን በቴዲ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

በተጨማሪ ከአራት ዓመት በፊት በተፈረመው ውል ላይ ከስልክ ድምጽ ማሳመሪካ CRBT የሚገኝ ገቢ ለሰዋሰው እንዲሰጥ የሚፈቅደውን ስምምነት ማሻሻያ እንዲደረግበት በቴዲ የቀረበው ጥያቄ ከሰዋሰው ይሁንታ አላገኘም።

ልዩነቶቹ ሊጠቡ ባለመቻላቸውና የአልበሙ መውጫ በመድረሱ ሁለቱም ወገኖች ውሉን በስምምነት አቋርጠዋል።

ውሉ ሲፈረም ሰዋሰው ለቴዲ አጠቃላይ 50 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ተስማምቶ ነበር። የዚህንም ግማሽ 25 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ተከፍሎት ነበር።

አልበሙ እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረው ከአራት አመት በፊት የነበረ ቢሆንም በተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት ውሉ ሊታደስ አልቻለም። በመጨረሻም ውሉ በሰላማዊ መግባባት ፈርሷል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ቴዲና አሳታሚው ድርጅት ውይይት አድርገው ውሉን ለማደስ ባለመግቤታችው ቴዲ ወስዶት የነበረውን 25 ሚሊዮን ብር ከአራት አመት የባንክ ወለድ ጋር ታሳቢ ተደርጎ 33 ሚሊዮን ብር ለሰዋሰው መመለሱን የአርቲስቱ የማናጅመንት ባልደረባ ተናግረዋል።

ሰዋሰው መልቲሚዲያም አርቲስቱ የወሰደውን ግማሽ ክፍያ 25 ሚሊዮን ብር ከአራት አመት የባንክ ወለድ ጋር ጨምሮ መመለሱን አረጋግጧል።

አሳታሚው ” በስራ ሂደት በሚያጋጥሙ ሃሳቦች ምክንያት ውሉ በስምምነት ነው የተፈረሰው ” ብሏል።

ቴዲ አፍሮ ” ኢትዮሪካ ” የተሰኘው አልበሙን ነገ ሀሙስ ሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ በራሱ ዩትዩብ ቻናል እንዲሁም በተለያዩ የማዳመጫ አማራጮች ለህዝብ ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

አልበሙ ቅዳሜ ይወጣል ቢባልም ቀደም ብሎ እንዲወጣ የተወሰነው በቴዲ አፍሮ መሆኑን እንዲሁም የወር ፣ የቀን እና ሰዓቱ ቁጥር ግጥምጥሞሽ አርቲስቱ በምክንያት ያደረገው መሆኑን የማናጅመንት ክፍሉ ለ” ኢትዮፒካሊንክ ” የመዝናኛና መረጃ ፕሮግራም አሳውቋል።

NB. ስምምነቱ ሊፈርስ ስለቻለበት ምክንያት እና አርቲስቱ ስለመለሰው የገንዘብ መጠን ሙሉ መረጃው የተወሰደው ከ ” ኢትዮፒካሊንክ ” የሬድዮ ፕሮግራም ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ...

በ’ፊንቴክ’ የማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩት ላይ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጠ

በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ስም በተፈጸመ  የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር...

የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት የኢንቨስመንት መጠን 723 ሚሊዮን ዩሮ መድረሱ ተሰማ

ከ20 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች  በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን...

የቴሌግራም ማስጠንቀቂያ

ቴሌግራም (Telegram) ኦፊሴላዊ ያልሆኑ የቴሌግራም መተግበሪያዎችን (Unofficial Apps) በሚጠቀሙ...