በአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን የ2026 ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በብራዛቪል የተገናኙት የልማት ፋይናንስ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና ስራ ፈጣሪዎች፤ የግል ኢንተርፕራይዞች እና የውስጥ ቀጣናዊ ንግድ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን ዋና ሞተሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በባንኩ ቡድን የተደራጀው የዚህ የግል ዘርፍ መድረክ የተካሄደው “የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን በማልማት ረገድ የግል ኢንተርፕራይዞች ሚና እና ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ የእሴት ሰንሰለቶች ኢንዱስትሪላይዜሽን እና በውስጥ ቀጣናዊ ንግድ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች መዋቅራዊ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል ነው።
በአፍሪካ በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች ውስጥ የግል ዘርፉ ከ80 በመቶ በላይ የመንግስትን ገቢ እና ከ90 በመቶ በላይ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ከጠቅላላው የግል ድርጅቶች ውስጥ 90 በመቶውን ይሸፍናሉ።
ሆኖም ግን፣ በአብዛኛው በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ ወደ ትላልቅ ኢንተርፕራይዞች ማደግ የቻሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል።
