በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የበለጸገው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ጥቆማ መስጫ የሞባይል መተግበሪያ በዓለማቀፍ ደረጃ ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ በመሆን መመረጡ ተገልጿል፡፡
መተግበሪያው ከግንቦት 13 እስከ 15 (እ.ኤ.አ) በዱባይ በሚካሄደው ዓመታዊ የዓለም ፖሊስ ጉባኤ (World Police Summit) ላይ በተለያየ ዘርፍ ለተሸላሚነት ከተመረጡት መካከል አንዱ ሆኗል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመተባበር ያበለፀገው የወንጀል ጥቆማ መስጫ የሞባይል መተግበሪያ (EFPApp) ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ (Best Police Application) በተባለው ምድብ አንደኛ ደረጃን መያዙም ነው የተነገረው።
ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው ጉባኤ በምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ ውድድር ላይ ከተለያዩ ሀገራት ስማርት የፖሊስ መተግበሪያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ውድድሩ በፈጠራ፣ በንድፍ፣ በቴክኖሎጂ እና በተጽእኖ ፈጣሪነት መስፈርቶች መተግበሪያዎቹን አወዳድሯል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ጥቆማ መስጫ የሞባይል መተግበሪያም በኤ.አይ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ለአጠቃቀም ምቹ እና ለማህበረሰባዊ ደህንነትም ጉልህ ሚናን በመጫወቱ በዓለማቀፍ ደረጃ ውድድሩን ማሸነፉ ተነግሯል።
መተግበሪያዉ ዜጎች በሞባይል ስልኮቻቸው አማካኝነት ካሉበት ሆነው የወንጀል ጥቆማ ለፖሊስ ለመስጠትና የደረሰበትን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስርዓት ነው።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ላይ ተግባራዊ ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያገነነው መረጃ ያመለክታል።
ይህ እውቅና ኢትዮጵያ ወንጀልን በመከላከል ዘርፍ ቴክኖሎጂን በማጣመር ዘርፉን ለማዘመን እያደረገች ያለው ጥረት ስኬታማ እንደሆነ የሚያሳይመሆኑም ተገልጿል፡፡
መተግበሪያው ዜጎች ሲፈፀም የሚያዩትን ወንጀል በፎቶ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ እና በሌሎች አማራጮች በማስቀረት በቀላሉ ጥቆማ ማቅረብ የሚችሉበት ሲሆን፤ የተጠቆመው የወንጀል ድርጊት የደረሰበትን የምርመራ ሂደት ለመከታተልም ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
ይህም መተግበሪያ የተለያዩ የቋንቋ አማራጮችን ማለትም፤ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፍ ሶማሊ እና እንግሊዝኛን በውስጡ የያዘም ሲሆን፤ ለዐይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸው ምቹ አገልግሎት እንዳለው ተመላክቷል፡፡
(አሐዱ ሬዲዮ)
