በከበረች በግንቦት አንድ ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች። እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት፡፡ ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ፡፡
ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ። በዚያ ወራት የመካኖች መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና፡፡ እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር፡፡ ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ሐሳባቸውን ተመለከተ፡፡
ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው፡፡
በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ፤ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት። ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች፡፡
ከዚህም በኋላ ይህችን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች። ከአይሁድ ለማምለጥ የተሰደዱት ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአድባረ ሊባኖስ ሥር ግንቦት አንድ ቀን ወለዷት፡፡
ስሟንም ‹ማርያም› ብላ ሰየመቻት። ትርጓሜውም ‹እመቤት› ነው። ‹ደግሞም ሀብታና ስጦታ› ማለት ነው፡፡ በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት ናትና።
በንጽሕናዋ እና በቅድስናዋ ተደንቀው ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም ያመሰግኗታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡
የሕይወት ክርስቶስ እናት ዛሬ ተወልዳለችና፡፡ በሥርዓት ቤተ ክርስቲያን መሠረት በቀናች በተዋሕዶ እምነት ሆነን፤ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን ድንግል ማርያምንም እያመሰገንን ልናከብረው ይገባል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ አሜን!
