የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው የግብርና ምርቶች በኢትዮጵያ

Date:

ከ20 ዓመታት በፊት የተዋወቀው በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶች (GMO) ጥቅም ላይ ማዋል በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ክርክሮች የተነሱበት ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያም ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ መከራከሪያ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከሙከራ በዘለለ የጥጥ ምርት ቀደም ብሎ እንዲሁም የበቆሎ ምርት ደግሞ በቅርቡ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ ተሰጥቷል።

በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተደረገ ምሁራዊ ክርክር መድረክ ላይ በተወያይነት የቀረቡት ፕ/ር ፍሬው በGMO ላይ የሚነሱት ክርክሮች ” ያለቀ ጉዳይ ነው ” ሲሉ በተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ተቀብለዋቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ ፕ/ር ጥልዬ ፈይሳ ” የGMO ጉዳይ በህክምና ብዙ ጥያቄ አይነሳበትም ለምሳሌ ኢንሱሊን የሚመረተው በዚሁ መንገድ ነው ” ሲሉ በምርት ደረጃ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2024 ብቻ 209.8 ሄክታር መሬት በዚሁ ምርት መሸፈኑን ገልጸዋል።

ጥቅሙንም ሲያስረዱ ” ምርት ይጨምራል፤ በተባይ ለሚጠቁ ሰብሎች መፍትሔ ይሆናል ” ሲሉ አንስተው ተከራክረዋል። ለምሳሌም የጥጥ ምርት በተባይ በጣም ስለሚጠቃ ምርቱ እና ጥራቱ የወረደ ነበር ዘረመል ልውጥ የጥጥ ምርት (BT Cotton) ግን ይሄንን መቋቋም የቻለና ውጤታማ መሆኑን ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ የሙከራ ምርቱን የጨረሰው ድርቅና ተባይ ይቋቋማል የተባለው የበቆሎ ዝርያም በምርቱ ” 56 በመቶ የምርት ጭማሬ አሳይቷል ” ሲሉ በተለይም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ማብራሪያ ላይ አንስተዋል።

በተቃራኒ ጎራ ሆነው ሲሞግቱ የነበሩት ዶ/ር ጸደቀ ግን በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶች ” ምርት አይጨምሩም ይህንን አምራቾቹም በራሳቸው አይናገሩም ” ሲሉ መከራከሪያ ሀሳባቸውን አንስተዋል።

” ልማትን በሦስተኛ ወገን ልታስብ አትችልም ” የሚሉት ዶ/ር ጸደቀ ” ምርት ይጨምራል የሚለውም ምርት አይጨምርም ማናጅመንቱ ነው በሙከራ ላይ ምርት እንዲጨምር የሚያደርገው ” ሲሉ ሀሳባቸውን አንስተዋል።

” ያለንን ቴክኖሎጂ አሟጠን አልተጠቀምንም ” ፤ ” የገበሬው ምርት እና ጥናቱ መካከል ልዩነት አለ ” ፤ ” አንዴ ከገባንበት ደግሞ መመለሻው ከባድ ነው ” ፤ ” የተቋማት ጥገኝነት ያመጣል (Corporate Dependency) ” የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦችን አስቀምጠው ሞግተዋል።

በክርክር መድረኩ GMO ደግፈው የተሳተፉት ፕ/ር ፍሬው መክብብ፣ ፕ/ር ጥልዬ ፈይሳ እና ዶ/ር ታደሰ ዳባ ፣ ዶ/ር ጸደቀ አባተ ያነሷቸውን ነጥቦች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፦

– ለገበሬው አማራጭ እንስጠው፤
– የሦስተኛ ወገን ጫና ሳይሆን በራሳችን ፈልገን መርምረን ጥቅምና ጉዳቱን አገናዝበን ነው ጥቅም ላይ የዋለው፤
– ምርት እንደሚጨምር ISAA ጨምሮ ሌሎች በጥናት ያረጋገጡት ነው፣ ሳይንስን መሰረት አድርገን መነጋገር አለብን በቂ ጥናት ተደርጓል፤
– ከዋጋ አንጻር የጸረ ተባይ መድኃኒት ዋጋን ይቀንሳል፣ ተመራጭ ነው፤
– ሀገሪቱ ይህንን መቆጣጠር የሚችል ህግና የተቋቋመ ተቋም አለ፤
– የጥጥ ምርትን ገበሬው ፈልጎት ማንም ሳያስገድድው እየተጠቀመ ያለው የሚሉ ሀሳቦችን አንጸባርቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ዘንድ ሁለቱንም ጎራ የሚመለከቱ ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል።

ኢትዮጵያ በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶችን (GMO) መጠቀም አለባት የለባትም የሚለው ክርክር ወደ መደብዘዙ የሄደ ቢመስልም አሁንም ይህንን የሚሞግቱ ሙሑራን ግን አልጠፉም ፤ ማኅበረሰቡም ከስጋት የተላቀቀ አይመስልም።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በተከታተለው በዚህ ምሁራዊ ክርክር መድረክ ላይ በኢትዮጵያ በእንሰት ላይ እንዲሁም በጎመን ዘር ላይ የዘረመል ምህንድስና ዘዴን ተጠቅሞ ባክቴሪያን የሚቋቋም እንሰት እና ለዘይት ምርት የሚሆን ጎመን ዘር የማምረት ሂደት በሙከራ ላይ እንደሚገኙ ሰምቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...