የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) የኢትዮጵያ መንግስት የሦስት የሮይተርስ ጋዜጠኞችን የሥራ ፈቃድ እንዲመልሱ ጥሪ አቀረበ።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሦስት የሮይተርስ ጋዜጠኞች የሥራ ፈቃድ አለማደሱ እና 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን እንዲዘግቡ የተሰጣቸውን ፈቃድ መሰረዙ ይታወሳል።
እርምጃዉ የተወሰደው የዜና ወኪሉ ኢትዮጵያ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላት ማሰልጠኛ ካምፕ ገንብታለች የሚል የምርመራ ዘገባ ካወጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ ድርጊቱን “በዓለም አቀፍ እና በገለልተኛ ፕሬስ ላይ እየታየ ያለ አሳሳቢ የጭቆና እና የቁጥጥር እርምጃ አካል ነው” ብለዋል፡፡
ባለሥልጣናቱ የሮይተርስን የሥራ ፈቃድ እንዲመልሱ እና ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን እንደ ስጋት ከመመልከት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
