በኢትዮጵያ በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ዘዴዎች አማካኝነት የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶችና የማጭበርበር ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመራቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አስታወቀ።
ኢንሳ በመግለጫው፡- የሳይበር ወንጀለኞች በሀገሪቱ የሚካሄዱ ታላላቅ ሲምፖዚየሞችንና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዜጎችን መረጃና የባንክ ሂሳብ እየመዘበሩ ይገኛሉ ብሏል።
አክሎም፤ አጥቂዎቹ በተለይም “ነጻ የኢንተርኔት ፓኬጅ”፣ “ልዩ የሥራ ቅጥር” ወይም “የስብሰባ መሳተፊያ ሊንክ” የሚሉ አሳሳች የማኅበራዊ ሚድያ ማስፈንጠሪያዎችን በማሰራጨት ተጠቃሚዎች እንዲጫኑት በማድረግ የጥቃት እርምጃ ይወስዳሉ ሲል አብራርቷል።
ተጠቃሚዎች የተላከላቸውን ሊንክ ሲጫኑ ወይም ሚስጥራዊ ኮድ ሲሞሉ፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ወዲያውኑ በጠላፊዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚውል አስተዳደሩ በጥብቅ አሳስቦ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል።
ወንጀለኞቹ አንድ ጊዜ የአንድን ግላብ ሰው አካውንት ከተቆጣጠሩ በኋላ የተጎጂውን ስም በመጠቀም ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶቹ “ድንገተኛ ችግር አጋጥሞኛል” የሚሉ የሐሰት የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን በመላክ ከፍተኛ ዝርፊያ እየፈጸሙ እንደሆነ አስታውሷል።
ይህ ድርጊት ከግለሰቦች ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ባለፈ፣ ሚስጥራዊ መረጃዎች በጠላፊዎች እጅ እንዲወድቁ በማድረግ በሀገር ደኅንነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑ ተገልጿል።
ይህንን ስጋት ለመከላከል ማኅበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰበው ኢንሳ፤ ማንኛውም ተጠቃሚ በመተግበሪያዎቹ ላይ የሁለትዮሽ ማረጋገጫ (Two-Step Verification) በአስቸኳይ እንዲተገብር መክሯል።
ከማይታወቁ አድራሻዎች የሚላኩ ማስፈንጠሪያዎችን ካለመክፈት ባለፈ፣ አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሱ ወዲያውኑ “Report” እና “Block” በማድረግ ስርጭቱን መግታት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል ወይም በስልክ የሚላክ የማረጋገጫ ኮድ ለማንኛውም አካል አሳልፎ አለመስጠት ለዲጂታል ደኅንነት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እነዚህን ወንጀለኞች በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ከጸጥታና ፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ዜጎች ማንኛውም የጥቃት ሙከራ ሲያጋጥማቸው በነጻ ስልክ መስመር 933 በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ የሳይበር ደኅንነትን ማስጠበቅ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
