የሀገራችን አንጋፋ ሰዎች ሰለ መፅሐፍ ምን አሉ
በኢንስትራክተር ዳዊት መኮንን የተደረሰው እና የአካል ብቃት ዕንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩረው “አካልን በብቃት” የተሰኘ መጽሐፍ ሊመረቅ ስለመሆኑ ተገልጿል። መጽሐፉ በዓይነቱም ሆነ በይዘት “ለየት ያለ” ስለመሆኑ ተነግሯል።
መጋቢት 11 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ካፒታል ሆቴል ለመገናኛ ብዙሃን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፣ መጽሐፉ “የሕጻናት የአካል ብቃት ዕንቅስቃሴ እንደምን መከወን አለበት? የስነ ምግብ ስርዓት ምን መምሰል አለበት? ባሕላዊ ጭፈራ ከስፖርት ጋር ያለው ሳይንሳዊ መስተጋብር ምን ይመስላል?” በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን ተብራርቷል።
ደራሲው ኢንስተራክተር ዳዊት መኮንን በዚህ መጽሐፍ “እኔ ልቀድም እችላለሁ፤ በቀጣይ ግን እኔን ተከትለው የሚመጡ ጸሐፊያን ይኖራሉ” ሲል አመልክቷል።
አክሎም፣ “የ’ለታሪክ አድቨርታይዚንግ’ ባለቤት አቶ ለታሪክ ዓለማየሁ በብዙ አግዞኛል፤ መጽሐፉን እንዳዘጋጅም አነሳስቶኛል” ያለው ደራሲው፣ “ለፍላጎቴ ስል ታግያለሁ፤ አሁን እታገላለሁ፤ ወደፊትም እታገላለሁ” በማለት አጽንዖት ሰጥቷል።
የ”ለታሪክ አድቨርታይዚንግ” ባለቤት እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ለታሪክ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ የመጽሐፍ ስራ አድካሚ መሆኑን በማንሳት፣ የኢንስትራክተር ዳዊት ሁለተኛ መጽሐፉን ለማሳተም ዕገዛ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም፣ ለንባብ የበቃውን ሶስተኛ አዲስ መጽሐፍ ለማሳተም እና ለሌሎች ስራዎች ድጋፋቸውን እንዳልሰሰቱ በማብራራት፣ “የወረቀት ወጪ እጅግ በጣም ውድ መሆኑን ሕብረተሰቡ እና መንግስት ይወቅልን። በዚህ መጽሐፍ ደራሲውን ለማገዝ ያህል ነው የተሳተፍነው” ብለዋል።
“ሁሉንም በአጠቃላይ ማገዝ ባይቻልም፣ የተወሰነውን ለማገዝ አላዳገተንም” ያሉት አቶ ለታሪክ፣ “አካልን በብቃት” በይዘቱም ሆነ በዓይነቱ ለየት ያለ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
መጽሐፉ በአስራ አንድ ምዕራፎች የተዋቀረ እና 260 ገጾችን የያዘ ሲሆን፣ በ”ለታሪክ አድቨርታይዚንግ” አማካይነት ሲታተም፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የባለቀለም ሕትመትን ተግባራዊ የተደረገበት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአጠቃላይ ለመጽሐፉ መታተም 2.8 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲደረግበት፣ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ከቀኑ 10:00 ጀምሮ እንደሚመረቅ ተጠቁሟል።
በ3 ሺሕ ያህል ኮፒ ታትሞ ለአንባቢያን የቀረበው ይህ መጽሐፍ፣ የሽፋን ዋጋው 1 ሺሕ 199 ብር መሆኑን እና ይህ ዋጋ መጽሐፉ “የወጣበትን ወጪ ለመመለስ ሳይሆን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያህል” ተብሎ እንደተተመነ ተመላክቷል።
ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አርቲስት አመለሰት ሙጬ፣ የአምባሳደር ልብስ ስፌት መስራች እና ባለቤት አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን፣ የካልዲስ ኮፊ ባለቤት ጸደይ አስራት እና ተዋናይ ሄኖክ ወንድሙ በመጽሐፉ ላይ የጀርባ አስተያየት የሰጡ ዕውቅ ሰዎች ናቸው።
እንዲሁም መጽሐፉን በመተግበሪያ፣ በአማዞን መተግበሪያ አማካይነት በመላው ዓለም ለሚገኙ አንባቢያን በአማዞን እንደሚቀርብ እና በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች መጽሐፉን በመተርጎም እንዲዳረስ መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል።
ኢንሰትራክተር ዳዊት ከዚህ ቀደም “የስፖርት ማሽን አጠቃቀም” በሚል ርዕስ የመጀመሪያ መጽሐፉን ያሳተመ ሲሆን፣ ሁለተኛ መጽሐፉን ደግሞ “ስፖርት ያለመሳሪያ” በተሰኘ ርዕስ በማሳተም ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡
