ኢትዮጵያ ልታስገነባው ላቀደችው ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚመረጡ ኮንትራክተሮች፣ ከግንባታ ብቃታቸው በተጨማሪ የራሳቸውን የፋይናንስ ምንጭ (Funding) ይዘው እንዲመጡ ቅድመ ሁኔታ መቅመጡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
በአየር መንገዱ አዲስ አቅጣጫ መሰረት፣ የግንባታ ጨረታውን የሚያሸንፉ ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቱን የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን አበዳሪ ባንክ አብረው ይዘው እንዲመጡ ተጠይቀዋል።
ይህ መንግስት፣ አበዳሪዎች እና ኮንትራክተሮች በጋራ የሚሳተፉበት የሦስትዮሽ የፋይናንሲንግ ሞዴል፣ የብድር ሂደቱን ይበልጥ ፈጣንና ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተሰምቷል።
እንደ ሌሎቹ የመንግስት ብድሮች ቀጥተኛ ያልሆነው ይህ የኤርፖርት ግንባታ ብድር፣ “ውስብስብና ብዙ ጠመዝማዛ መንገዶች ያሉት” ተብሎ ተገልጿል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰዉ ለተቋሙን ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ባቀረቡት ወቅት እንደተናገሩት፤ ብድሩን የሚወስደው በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳይሆን፣ ለዚሁ ፕሮጀክት ተብሎ ራሱን ችሎ የሚቋቋም ልዩ ድርጅት ነዉ።
ለብድሩ ዋስትና ተደርጎ የሚቀርበውም ራሱ የሚገነባው ኤርፖርት መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዉ አስረድተዋል።
ለአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ በአጠቃላይ 9 ቢሊየን ዶላር ገደማ ከብድር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን ባለው ሂደት በሞሮኮ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ የተለያዩ አበዳሪ ድርጅቶች እስከ 6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎታቸውን መግለጻቸውን ለመረዳት ችሏል።
“አበዳሪዎች በፕሮጀክቱ አዋጭነት ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው በፓሪስ፣ ለንደን፣ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሰፊ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል” ሲሉ አቶ መስፍን ጣሰዉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን በፋይናንስ ረገድ ውጤታማ ለማድረግ የአፍሪካ ልማት ባንክ በዋና አስተባባሪነት የተሰየመ ሲሆን፣ ኬፒኤምጂ እንደ ፋይናንስ አማካሪ በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የአዋጭነት ጥናቱ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ለአበዳሪዎች የተሰጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቶቹ ተጨማሪ መረጃዎችን እየገመገሙ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በቢሾፍቱ አቅራቢያ ‘አቡሴራ’ በተባለ አካባቢ የሚገነባው ይህ አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. መሰረተ ድንጋይ መቀመጡ የሚታወስ ሲሆን አጠቃላይ የብድር ስምምነቱና ውሳኔው እስከ መጪው ታህሳስ 2026 (እ.ኤ.አ) መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
capital news
