ኢትዮ ቴሌኮም የሀገሪቱን ዲጂታል መሠረተ ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት በባርሴሎናው ዓለም አቀፍ የሞባይል ኮንግረስ ላይ ከኤሪክሰን ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።
ይህ ስትራቴጂያዊ ስምምነት የኩባንያውን የሦስት ዓመት የ”ቀጣዩ አድማስ” ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ በኤሪክሰን የኔትወርክ አስተዳደር ቀጠና ውስጥ በሚገኙ 1,500 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ እና የማሻሻያ ሥራዎችን ያካትታል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ነባር መሠረተ ልማቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተካት የ4ጂ ሽፋንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግና የ5ጂ ተደራሽነትን በማስፋፋት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚረዳ የፍጥነት ኮኔክቲቪቲን ዕውን የሚያደርግ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኩባንያው እንዳስታወቀው ፤ 75 ለሚሆኑ የገጠር አካባቢዎች ተስማሚ የሞባይል ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብና 502 ነባር የ3ጂ ጣቢያዎችን ወደ 4ጂ ለማሳደግ ያስችላል።
በዚህም የ4ጂ ኔትወርክ የመሸከም አቅም በ2.8 ሚሊዮን አድጎ አጠቃላይ አቅሙን 4.1 ሚሊዮን እንደሚያደርሰው ታውቋል።
በተጨማሪም የኤልቲኢ አገልግሎት ወደ 157 ተጨማሪ ከተሞች በመስፋፋቱ አጠቃላይ የሕዝብ ሽፋኑን በ45 በመቶ እንደሚያሳድገው ተገልጿል።
